ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የዘጠኝ ወራት እቅድ አፈፃፀም ከማኔጅመንት አባላት ጋር ግምገማ ማካሄድ ጀመረ፡፡
ሚያዚያ 2/2017 ዓ.ም
አዳማ
የኢትዮጵያ ፀረ-አበረታች ቅመሞች ባለስልጣን በ2017 በጀት አመት የ9 ወራት የእቅድ አፈጻጸም ላይ ከተቋሙ ከፍተኛ አመራር ከማኔጅመት አባላት ጋር በአዳማ ከተማ የጋራ የውይይት መድረክ እያካሄደ ይገኛል ።
ለሶስት ቀናት በሚቆየው በዚህ መድረክ የዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈጻጸም ማየት እና የትኩረት አቅጣጫዎችን ማስቀመጥ ፣ በበጀት ዓመቱ በክፍተት የተለዩ ጉዳዮችና ያሉበት ሁኔታ መፈተሽ እንዲሁም በተቋም ደረጃ የተዘጋጁ መመሪያዎችን የማፅደቅ ዋነኛ ጉዳዮች እንደሚሆኑ ይጠበቃል፡፡
የውይይት መድረኩን የመሩት የኢትዮጵያ የፀረ-አበረታች ቅመሞች ዋና ዳይሬክተር አቶ መኮንን ይደርሳል እንደተናገሩት እያንዳንዱን ሥራ አፈፃፀማችንን በጥልቀት በመገምገም በቀጣይ መሻሻል እና መጠናከር ያለባቸውን ጉዳዮችን በአግባቡ ለይተን ውጤት የሚያመጣ ግምገማ መሆን መቻል ይኖርበታል ብለዋል ።
በዚህም እንደ ተቋም የታዩ መልካም አፈጻጸሞችን በተገቢው ሁኔታ በማስቀጠል በቀጣይ በሚቀሩን ወራት በአፈጻጸም ወቅት ሳይከናውኑ የቀሩ ተግባራትን በማስተካከል መስራት እንደሚገባ ጠቁመዋል ፡፡
አያይዘውም ሁሉም አመራሮች የነቃ ተሳትፎ ማድረግ እንደሚገባቸው ገልፀው ተቋሙን ወደ ፊት የተሻለ አፈፃፀም እንዲኖረው ሥራዎችን በተደራጀና በተቀናጀ መንገድ መስራት እንደሚገባ ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡
በመድረኩም የተቋሙ የዘጠኝ ወራት እቅድ አፈጻጸም እና የክትትልና ግምገማ ግብረ መልስ በስትራቴጂክ ጉዳዮች ስራ አስፈጻሚ ቀርቦ በመቀጠልም በየሥራ ክፍሎች ያከናወናቸው አፈፃፀም በማቅረብ የጋራ ውይይት ተደርጎባችዋል።





