የአለም አቀፉ አመታዊ የፀረ-ዶፒንግ ጉባኤ (WADA’s Annual Symposium) እ.ኤ.አ ከመጋቢት 18/2025 ጀምሮ ላለፉት ቀናት በስዊዘርላንድ ሉዛን ከተማ ተካሄዷል።
አገራችን ኢትዮጵያን በመወከል በዚህ ጉባኤ ላይ የተሳተፍን ሲሆን በስብሰባው ላይ ከቀረቡት የጋራ ኃሳቦች ባሻገር በየደረጃው እየተካሄደ የሚገኘውን አጠቃላይ የፀረ-አበረታች ቅመሞች እንቅስቃሴ የበለጠ ማጠናከር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ከተለያዩ አገራትና አለም አቀፍ ተቋማት የስራ ኃላፊዎች ጋር ውይይቶችን አካሂደናል።
በተለይም ከአለም አቀፉ የፀረ-ዶፒንግ ኤጀንሲ (WADA) ልዩ ልዩ የስራ ክፍል ኃላፊዎች፣ ከአለም አትሌቲክስ የኢንተግሪቲ ዩኒት (AIU) አመራሮችና ባለሞያዎች፣ ከተለያዩ አቻ አገራት የፀረ-ዶፒንግ ተቋማት አመራሮችና ተወካዮች፣ ከዶፒንግ ምርመራ ላቦራቶሪ አመራሮች፣ ከተለያዩ የምርመራ ቁሳቁስ አቅራቢ ድርጅቶችና የመሳሰሉት አለም አቀፍ ተቋማት ጋር የተናጠልና የጋራ ውይይቶችን አካሂደናል። በቀጣይም ትኩረት አድርገን በምንሰራባቸውና የሁለትዮሽ ግንኙነት በሚፈልጉ ጉዳዮች ዙሪያም መግባባት ላይ ደርሰናል።
ከዚህም በተጨማሪ ከሉዛን የአበረታች ቅመሞች ወይም ዶፒንግ ምርመራ ላቦራቶሪ አመራሮችና ባለሞያዎች ጋር የሁለትዮሽ ውይይትና በላቦራቶሪው ተገኝተን ጉብኝት ያካሄድን ሲሆን በአገራችን ላቦራቶሪ ለማቋቋም ለጀመርነው እንቅስቃሴም እስከ ስልጠና የሚደርስ የቴክኒክ ድጋፍ እንደሚያደርጉልን ማረጋገጥ ችለናል።





