“የፀረ-አበረታች ቅመሞች ጉዳይ ለአትሌቶች ከየትኛውም አጀንዳ በላይ ተቀዳሚ አጀንዳ ሊሆን ይገባል”
አቶ መኮንን ይደርሳል
***********************
ታህሳስ 8/2018 ዓ.ም.
አዲስ አበባ
አገራችን ኢትዮጵያ በዓለም-አቀፍ ደረጃ ተወዳድረው አስደናቂ ውጤቶችን ያስመዘገቡና ስሟን ከፍ አድርገው ያስጠሩ ብርቅዬ አትሌቶች ባለቤት ናት። ውጤቱ ዘመናዊ የስፖርት ስልጠና፣ በቂ ትጥቅ እና የደሞዝ ክፍያ በሌለበት የአገርን ክብር እና ፍቅር ብቻ በማስቀደም በላብ፣ በጥረት፣ በትጋት እና በተፈጥሯዊ መንገድ ብቻ የተመዘገበ መሆኑ ከሁሉም በላይ አስገራሚ ያደርገዋል።
ይሁን እንጅ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አገራችን በስፖርቱ የገነባችውን መልካም ስም የሚያጎድፍ፤ ቀደምት አትሌቶቻችንም ያስመዘገቡትን ድል በጥርጣሬ እንዲታይ የሚያደርጉ እና ከአርአያነት ያፈነገጡ ተግባራት በአንዳንድ አትሌቶች እና አካላት ተስተውለዋል። የኢትዮጵያ ፀረ-አበረታች ቅመሞች ባለስልጣንም ጉዳዩ ስር ከመስደዱ እና በአገራችን ስፖርት ላይ ውስብስብ ችግር ከመፍጠሩ በፊት የተለያዩ የመከላከያ እና የመቆጣጠሪያ ስልቶችን ቀርፆ ሲንቀሳቀስ ቆይቷል። በዚህም ጉዳዩ ይበልጥ እንዳይባባስ እና እንዲገታ ከማድረግም ባለፈ በዓለም-አቀፉ የፀረ-አበረታች ቅመሞች መመዘኛ ብቁ (Compliant) በመሆን በዓለም-አቀፍ ደረጃ ለሚገኙ አቻ ተቋማት ምሳሌ መሆን የሚችል ተግባራትን ማከናወን ችሏል።
ባለስልጣን መ/ቤቱ የመከላከል ተግባሩን አጠናክሮ በመቀጠል በአትሌቲክስ ስፖርት በማናጀሮች ስር ለሚገኙ አትሌቶች የፀረ-አበረታች ቅመሞች የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠናዎችን በመስጠት ላይ ይገኛል። ከዚህም ጋር በተያያዘ በግሎባል ስፖርት ስር ለሚገኙ አትሌቶች የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠናው የተሰጠ ሲሆን፤ በስልጠናው መክፈቻ ላይ የባለስልጣን መ/ቤቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ መኮንን ይደርሳል የፀረ-አበረታች ቅመሞች ጉዳይ ለአትሌቶች ከማንኛውም አጀንዳ በፊት ተቀዳሚ አጀንዳ ሊሆን እንደሚገባ አፅእኖት ሰጥተው አብራርተዋል። ዋና ዳይሬክተሩ አክለውም፡- “አትሌቶች የህግ ጥሰት ፈፅመው ሲገኙ የቅጣት ውሳኔ እንዲተላለፍባቸው የሚደረገው አትሌቶቻችንን ስለማንወዳቸው ሳይሆን ከሁሉም በላይ የአገራችን ስፖርት ጉዳይ ስለሚያሳስበን እና አገርን ማዳን ስለሚጠበቅብን ነው። ስለዚህ አትሌቶች፣ አሰልጣኞች እንዲሁም ሌሎች አካላት ይህንን በአግባቡ ሊገነዘቡ ይገባል።” በማለት ገልፀዋል። በመጨረሻም በንፁህ ስፖርት መስፋፋት ዋነኛ ተጠቃሚ የምትሆነው በአንፃሩ ደግሞ በአበረታች ቅመሞች መስፋፋት ዋነኛ ተጎጂ የምትሆነው ኢትዮጵያ ናት። ከዚህም አንፃር አትሌቶች የቀደምቶቻቸውን ፈለግ መከተል እንደሚያዋጣቸው እና በተፈጥሯዊ መንገድ ማሸነፍ እንደሚቻል እምነትን ሊሰንቁ እንደሚገባ አሳስበዋል።
ስልጠናው በሁለት ክፍሎች ተከፋፍሎ፤ በመጀመሪያው ክፍል የፀረ-አበረታች ቅመሞች የህግ ጥሰቶች፣ የአበረታች ቅመሞች የወደፊት አዝማሚያ እና ስጋትን በተመለከት በአቶ ንጋቱ መኮንን በባለስልጣን መ/ቤቱ የውጤት አስተዳደር እና ህግ ትግበራ መሪ ሥራ-አስፈፃሚ እና በክፍል ሁለት በአቶ ፈለቀ ዋለልኝ አማረ በባለስልጣን መ/ቤቱ የአበረታች ቅመሞች መከላከል፣ ግንዛቤ ፈጠራ እና ህዝብ ንቅናቄ መሪ ሥራ-አስፈፃሚ ስለ ድጋፍ ሰጪ ምግቦች፣ የፀረ-አበረታች ቅመሞች የአሠራር ሥርዓቶች እና አበረታች ቅመሞች በሚያስከትሉት ጉዳትን በተመለከተ ሰፊ ማብራሪያ እና ገለፃ ተደርጓል።
በመጨረሻም ከሰልጣኞች ስለ አበረታች ቅመሞች የመገኛ አድረሻ፣ የስፖርት ድጋፍ ሰጪ ምግቦች (Supplements)፣ በአበረታች ቅመሞች ናሙና አሰባሰብ ሂደት እና መሰል ጉዳዮች ለተነሱ ጥያቄዎች በአሰልጣኞች እና በዋና ዳይሬክተሩ ማብራሪያ እና ምላሽ ተሰጥቶባቸው ስልጠናው ተጠናቋል።

