የአትሌት ማናጀሮች እና ተወካዮች የስፖርት አበረታች ቅመሞችን ወይም ዶፒንግን በመከላከልና በመቆጣጠር ረገድ የማይተካ ሚና እንዳላቸው ተጠቆመ፤ በአገራችን ለሚገኙ ሁሉም የአትሌቶች ድጋፍ ሰጭ ሰራተኞች ስልጠና ተሰጥቷል፡፡

ሰኔ 01/2010 ዓ.ም

በአገራችን ከዶፒንግ ነፃ የሆነ ስፖርት በማስፋፋት ጤናማ የሆኑና በትክክለኛው መንገድ ተወዳድረው የሚያሸንፉ አትሌቶችን ለማፍራትና በተለይም በአትሌቲክሱ ዘረፍ ቀደም ሲል ጀምሮ የተገነባውን መልካም ገፅታችንን ለማስቀጠል በየደረጃው የተለያዩ እንቅስቃሴዎች በመካሄድ ላይ መሆናቸው የሚታወቅ ሲሆን የአትሌት ድጋፍ ሰጭ ሰራተኞች ወይም ማናጀሮችና ተወካዮች በዶፒንግ መሰረታዊ ጉዳዮች ዙሪያ በቂ ግንዛቤ እንዲጨብጡ በማድረግ የበኩላቸውን ገንቢ አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱ በኢንተርኮንትኔንታል ሆቴል የጋራ ውይይት መድረክ ተካሂዷል፡፡

በውይይት መድረኩ ላይም በስፖርት አበረታች ቅመሞች መሰረታዊ ጉዳዮች፣ በፀረ-ዶፒንግ የተለያዩ የአደረጃጀት ሰንሰለቶች፣ በየደረጃው በተዘረጉ የአሰራር ስርዓቶችና የህግ ማዕቀፎች፣ በስፖርተኞች የህክምና አሰጣጥ፣ በስፖርተኞች አመጋገብ እና የስፖርት አበረታች ቅመሞች በሚያስከትሏቸው ማህበራዊ፣ የጤና፣ የስነ-ልቦና እና መሰል ተጓዳኝ ጉዳቶች ዙሪያ ገለፃ ተደርጓል፡፡

ከተሳታፊዎች ጋርም ውይይት የተካሄደ ሲሆን የስፖርት አበረታች ቅመሞችን ወይም ዶፒንግን በመከላከልና በመቆጣጠር ረገድ የአትሌቶች ማናጀሮችና ተወካዮች ሚና የጎላ መሆኑንና እነዚህ አካላት የበኩላቸውን ገንቢ ሚና መወጣት እንደሚገባቸው ተመላክከቷል፡፡

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳን አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረ-ስላሴ በመድረኩ ላይ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን የአትሌቲክስ ስፖርትን በጋራ ከዚህ ችግር ልንጠብቀው ይገባል ብለዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *