አትሌት እታፈራሁ ተመስገን ወዳጆ የተከለከሉ አበረታች ቅመሞችን መጠቀሟ በመረጋገጡ እና ሠነዶችን በማጭበርበር የ12 ዓመት ቅጣት ተጥሎባታል።
ቀን: ሰኔ 13/2012
   አትሌት እታፈራሁ ቀደም ሲል እ.ኤ.አ ጥቅምት 20/2019 ካናዳ ቶሮንቶ ላይ በተካሄደው የግል ማራቶን ውድድር ላይ ሁለት የተለያዩ የተከለከሉ የስፖርት አበረታች ቅመሞችን ወይም ዶፒንግ በመጠቀም ተጠርጥራ ላለፉት 8(ስምንት) ወራት ጉዳዩ በኢትዮጵያ ብሄራዊ የፀረ-አበረታች ቅመሞች ፅ/ቤት እና በአለም አትሌቲክስ የኢንተግሪቲ ዩኒት በጣምራ ሲጣራ ቆይቷል፡፡
   ስለሆነም በአትሌቷ ላይ በተደረገው ተጨማሪ ኢንቨስቴጌሽንና የማጣራት ተግባር በዚህ የግል ውድድር ላይ EPO (“r-EPO”) እና Testosterone የተባሉትን በስፖርት የተከለከለ አበረታች ቅመሞችን መጠቀሟ ተረጋግጧል፡፡ ከዚህም ባሻገር ፅ/ቤታችን ባካሄደው ኢንቨስቲጌሽን የተለያዩ የሐሰት ሰነዶችን በማዘጋጀት ተጨማሪ የማጭበርበር ተግባራት መከናወናቸውን ማወቅ ተችሏል።
ስለሆነም አትሌት እታፈራሁ የፈፀመችውን ተደራራቢ ጥፋት መሠረት በማድረግ እ.ኤ.አ ከህዳር 20/2019 ጀምሮ ለ12 ዓመታት በማንኛውም አገር አቀፍም ይሁን አለም አቀፍ ውድድር ላይ እንዳትሳተፍ የእገዳ ቅጣት ተጥሎባታል፡፡
   ከዚህም በተጨማሪ አትሌቷን በወንጀልም ጭምር ተጠያቂ ለማድረግ አስፈላጊ ሰነዶች በማሰባሠብና በማጠናቀር ወደሚመለከተው የህግ አካል እንዲተላለፍ ተደርጓል።
      በዚሁ አጋጣሚ ከኮረና ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ በየደረጃው የሚካሄዱት ስፖርታዊ ውድድሮች ለጊዜው የተቋረጡ ቢሆንም በአገራችን በየደረጃው የሚደረገው የስፖርት አበረታች ቅመሞች ወይም ዶፒንግ ክትትልና ቁጥጥር ግን ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል።
ስለሆነም ስፖርተኞች በዚህ ክፉ ወቅት ራሳቸውን ከኮሮና ወረርሽኝ እና ከስፖርት አበረታች ቅመሞች እንዲጠብቁ ፅ/ቤቱ ጥሪውን ያስተላልፋል፡፡
                                      የኢትዮጵያ ብሄራዊ የፀረ-አበረታች ቅመሞች ፅ/ቤት
                                                 

By Ermias

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *