የስፖርት አበረታች ቅመሞች የኢንተለጀንስና ኢንቨስቲጌሽን ቡድን ተቋቁሞ ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ተሸጋግሯል፡፡ በዚህ ቡድን ውስጥ ከኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን፣ ከኢትዮጵያ የምግብና መድኃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን፣ ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን፣ ከአዲስ አበባ የምግብና መድኃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን እና ከኢትዮጵያ ብሄራዊ የፀረ-አበረታች ቅመሞች ፅ/ቤት የተወጣጡ ባለሞያዎች እና አመራሮች ተካተዋል፡፡

ታህሳስ 24/2011 ዓ.ም

በአገራችን አበረታች ቅመሞችን ወይም ዶፒንግን በመከላከልና በመቆጣጠር ንፁህ ስፖርትን ለማስፋፋት እንዲሁም በአትሌቲክስ የተገነባውን መልካም ገፅታችንን ለማስቀጠል ቀደም ሲል ጀምሮ ዘርፈ-ብዙ ጥረቶች በመደረግ ላይ መሆናቸው ይታወቃል፡፡

በተለይም የተለያዩ የምርመራና ቁጥጥር ተግባራትን በማከናወን የተከለከሉ አበረታች ቅመሞችን በመጠቀምም ይሁን በሌላ መንገድ የህግ ጥሰቶችን በፈፀሙ አትሌቶች እና ፋርማሲዎች ላይ ከ2-4 ዓመት የሚደርሱ የቅጣት እርምጃዎች እንዲወሰዱ የተደረገ ሲሆን በቀጣይም ይህ ጅምር እንቅስቃሴ በተደራጀ መልኩ እንዲጠናከር ይደረጋል፡፡ ከዚህም ጋር ተያይዞ በአለም አቀፉ ስታንዳርድ መሰረት የምግብና መድኃኒት ቁጥጥር ባለስልጣንና የፖሊስ አካላትን ጨምሮ ጉዳዩ የሚመለከታቸውን የመንግስት ተቋማት ባሳተፈ መልኩ የኢንተለጀንስና ኢንቨስቲጌሽን ቡድን እንዲቋቋምና ኦረንቴሽን በመስጠት ወደ ተግባር እንዲገባ ተደርጓል፡፡

ይህ ቡድን በቋሚነት በአገራችን በተለያዩ አካላት የሚፈፀሙ የፀረ-አበረታች ቅመሞች ወይም ዶፒንግ የህግ ጥሰቶችን የሚመለከቱ መረጃዎችን በመሰብሰብ ሰፊ የኢንቨስቲጌሽን ተግባራትን ያከናውናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

የኢንተለጀንስና ኢንቨስቲጌሽን ውጤቶችን መሰረት በማድረግም በተለያየ መንገድ የህግ ጥሰት ፈፅመው የሚገኙ አካላት በአለም አቀፉ የፀረ-ዶፒንግ ህግ፣ በአገራችን የወንጀል ህግ አንቀፅ 526 እና በሌሎችም አግባብነት ባላቸው የህግ ድንጋጌዎች መሰረት ተጠያቂ እንዲሆኑ ይደረጋል፡፡

እስካሁን በተደረጉት እንቅስቃሴዎችም የተከለከሉ የስፖርት አበረታች ቅመሞችን ለአትሌቶች የሰጡ እና ህገ-ወጥ በሆነ መንገድ ያሰራጩ አካላት ተለይተው ጉዳያቸው በህግ በመታየት ላይ ይገኛል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *