የአትሌት ፍሬህይዎት ገሰሰን የፓሪስ ኦሊምፒክ ተሳትፎ በተመለከተ የተሰጠ መግለጫ
የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ነሐሴ 10/2016 በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አትሌት ፍሬህይወት ገሰሰ በፓሪስ ኦሊምፒክ ተመርጣ ሳትሳተፍ የቀረችው በኢትዮጵያ ፀረ-አበረታች ቅመሞች ባለስልጣን የዶፒንግ ምርመራ ሳይደረግላት በመቅረቱ እንደሆነ ገልጿል።
ከሁሉም በፊት የኢትዮጵያ ፀረ-አበረታች ቅመሞች ባለስልጣን በአገር አቀፍ ደረጃ አበረታች ቅመሞችን ወይም ዶፒንግን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የተቋቋመ Regulatory ተቋም ሲሆን ላለፉት ሰባት ዓመታት በህግ የተሰጠውን ይህንን ተግባርና ኃላፊነት ውጤታማ በሆነ መልኩ ሲፈፅም ቆይቷል። ይህንንም የአለም አቀፉ የፀረ-አበረታች ቅመሞች ኤጀንሲን (WADA) ጨምሮ የተለያዩ አለም አቀፍ ተቋማት ባደረጉት ክትትልና ግምገማ ያረጋገጡ መሆኑ ይታወቃል።
ባለስልጣን መ/ቤቱ የራሱን ተልዕኮ ከማሳካት ባለፈ በአለም አቀፍ ውድድሮች ላይ ለመሳተፍ ለኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ እና ለፌዴሬሽኖች የሚሰጣቸውን አስገዳጅ መስፈርት (Requirements) የማሟላት ተግባር ሲያከናውን ቆይቷል። ይህ ኃላፊነት የባለስልጣን መ/ቤቱ ግዴታ ባይሆንም በፓሪስ ኦሊምፒክም ከ160 በላይ አትሌቶችን በምርመራ ቋት ውስጥ በማካተት እ.ኤ.አ ከጥር 01/2024 ጀምሮ ለእያንዳንዱ አትሌት ከተቀመጠው መስፈርት ከእጥፍ በላይ ምርመራዎች ተደርገዋል። በድምሩም ከ744 በላይ ምርመራዎች ተካሂደዋል። በዚህም ሁሉም የብሄራዊ ቡድን አትሌቶች ምንም ችግር ሳይገጥማቸው ውድድራቸውን አድርገዋል።
ይሁን እንጅ አትሌት ፍሬህይወት ገሰሰ ከመጀመሪያው ጀምሮ በኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ የተሳታፊ አትሌቶች ዝርዝር (Ling Lists) በኋላ ደግሞ በዋናው የተሳታፊዎች ዝርዝር (Shortlist) ውስጥ ያልተካተተች በመሆኑ የአበረታች ቅመሞች ወይም ዶፒንግ ምርመራ አለም አቀፍ ስታንዳርዱን በጠበቀ መልኩ አልተደረገላትም። ዛሬ ደግሞ ጅራፍ ራሱ ገርፎ ራሱ ይጮሃል እንዲሉ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ በዝርዝሩ እንኳን ያላካተታትን አትሌት የዶፒንግ ምርመራ ስላልተደረገላት ሳትወዳደር ቀረች የሚል መግለጫ ሰጥቷል።
ይህ ፍፁም ስህተት ሲሆን አትሌቷ በኦሊምፒክ ውድድሩ ላይ ሳትሳተፍ የቀረችው በራሱ በኦሊምፒክ ኮሚቴው እንዝላልነት በተሳታፊዎች ዝርዝር ውስጥ አስቀድሞ ሳትካተት በመቅረቷና በየሶስት ሳምንቱ ሊደረግላት የሚገባውን ምርመራ ባለማሟላቷ መሆኑን ባለስልጣን መ/ቤቱ ያሳውቃል። ለዚህም ኦሊምፒክ ኮሚተው ኃላፊነቱን ሊወስድ ይገባል።
ከዚህም በተጨማሪ የባለስልጣን መ/ቤቱ ባለሞያዎችና አመራሮች በፓሪስ ኦሊምፒክ ውድድር ላይ በመገኘት ከዶፒንግ ጋር የተያያዙ ተግባራትን ማከናወን የሚጠበቅባቸው ቢሆንም የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ አስፈላጊውን የመግቢያ ካርድ (Accreditation) ሳያዘጋጅ በመቅረቱ ምክንያት ሳይሳካ ቀርቷል። በዚህም ምክንያት ብሄራዊ ቡድኑ በውድድሩ ላይ ችግር እንዳይገጥመው የon-line Platform በመጠቀም አስፈላጊውን አገልግሎት የመስጠትና ለአለም አቀፍ ተቋማት በየጊዜው ተገቢውን መረጃ የማድረስ ተግባራት ትኩረት ተሰጥቷቸው ተከናውነዋል። በዚህም ምክንያት በተቋም ደረጃ ዋጋ ከፍለንም ቢሆን አትሌቶቻችን ሳይቸገሩ ውድድራቸውን እንዲያጠናቅቁ ማድረግ ተችሏል።
ከዚህ ባለፈ የኢትዮጵያ ፀረ-አበረታች ቅመሞች ባለስልጣን በአለም አቀፍ ተቋማት ጭምር እውቅናን ያገኘ ውጤታማ ተግባር በማከናወን በግልፅ የሚታይ ውጤት በማስመዝገብ ላይ ይገኛል።
የኢትዮጵያ ፀረ-አበረታች ቅመሞች ባለስልጣን