ሀገር አቀፍ የፀረ – አበረታች ቅመሞች የምክክር መድረክ እየተካሄደ ይገኛል ፡፡
የአበረታች ቅመሞች ባለስልጣን ከኢፌድሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር እና ከኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በጋራ በመሆን ንፁህ ስፖርት ለሁለንተናዊ ውጤት በሚል መሪ ሃሳብ 1ኛው ሀገር አቀፍ የፀረ – አበረታች ቅመሞች የምክክር መድረክ ከባለድርሻ አካላት ጋር በዳማ ከተማ እየተካሄደ ይገኛል ፡፡
በመድረኩ ላይ ክቡር አባሳደር መስፍን ቸርነት የባህልና ስፖርት የኢፌድሪ ባህልና ስፖርት የስፖርት ልማት ዘርፍ ሚኒስቴር ዴኤታ ፣ የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የኪነጥበብ ስነ- ጥበብ ፈጠራ ልማት ዘርፍ ሚኒስቴር ዴኤታ ክብርት ወ/ሮ ነፊሳ አህመድ ፣ ፕሮፌሰር አክሊሉ አዛዥ የኢትዮጵያ የፀረ -አበረታች ቅመሞች ባለስልጣን ቦርድ ሰብሳቢ፣ የክልልና ከተማ አስተዳደር /አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንቶች፣ ከተለያዩ ተቋማት የመጡ ጉዳዮ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።
መድረኩን በእንኳን መጣችሁ በንግግር የከፈቱት ፕሮፌሰር አክሊሉ አዛዥ እንደተናገሩት ያለፉ ጀግኖች አትሌቶቻችንን የድል ታሪክ የሆነውን ታሪካችንን በበጎ መንገድ መጠበቅ ይገባናል ለዚህም ስፖርቱን እና የስፖርቱን ማህበረሰብ እየጎዳ ያለው የዶፒንግ ጉዳይ ከመቼውም ጊዜ በላይ አሁን ላይ ትኩረት ልንሰጠው ይገባል ብለዋል ፡፡
የአበረታች ቅመሞችን ተፅዕኖ ለመከላከል መንግስት ፅኑ አቋም በመያዝ በተቋም ደረጃ እንዲመራ በማድረግ የፀረ አበረታች ቅመሞች ባለስልጣንን በማቋቋም በሰው ሃይል፣ በላብራቶሪ ማደራጀት፣ ለማህበረሰቡና ለስፖርተኞች ግንዛቤ የመፍጠርና በምርመራ ውጤት የተገኘባቸውን በህግ እንዲጠየቁ የማድረግ ስራ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ያብራሩት ፕሮፌሰር አክሊሉ በቀጣይ የተጠናከረ ስራ ለመስራት በጥናትና ምርምር ላይ የተደገፈ ስራ እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል፡፡
የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የስፖርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አምባሳደር መስፍን ቸርነት ባስተላለፉት መልዕክት፡- የዶፒንግ ጉዳይ አሁን ላይ በአገር እና በአለም አቀፍ ደርጃ ተጽህኖ እያደገ መምጣቱ ለንጹህ ስፖርት መስፋፋት እና ማደግ ከፍተኛ ስጋት እየሆን መጥቷል ብለዋል፡፡
አገራችን ኢትዮጵያ ለስፖርት አመቺ የተፈጥሮ አየር እና ምግቦች ያላት በመሆኑ በተለይም በአትሌቲክሱ መስክ መሳተፍ ከጀመረች ጀምሮ በላባቸውና በጠንካራ ልምምዳቸው ታግዘው በአሸናፊነት የሚታወቁ ስመ ጥር አትሌቶች መፍለቂያ አገር ስትሆን ባለፉት ረጅም ዓመታት የተገኙት ውጤቶቻችን ከስፖርት አበረታች ቅመሞች አጠቃቀም ጋር ያልተያያዙ መሆኑን ይታወቃል።
የዶፒንግ ችግር እንደ አገር በአትሌቲክሱ እና በሌሎች ስፖርቶች ስጋት እየሆነ የሚገኝ ሲሆን በአሁን ወቅት አለም አቀፍ ውድድሮችን የምናካሂድበት ወቅት በመሆኑ የአገራችንን ውጤታማነት ለማስቀጠል መንግስት ለጉዳዮ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡
ክቡር ሚኒስትሩ አክለውም በአለም አቀፍ ደረጃ ውጤታማነትን ለማስቀጠል፣ የላቀ ብቃት ያላቸውን ስፖርተኞችን ለማፍራት እና የአገር ገጽታን ለመገንባት በዚህ ደረጃ ለመድረስ ከፍተኛ ጥረቶችን የሚጠይቅ በመሆኑ ይህን ታሳቢ በማድረግ የምክክር መድረኩ የዘጋጀ ሲሆን ሁላችንም በንቃት ልንሳተፍ ይገባል ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
በመቀጠልም የአበረታች ቅመሞችን የመከላከል እና መቆጣጠር እንቅስቃሴ ዳሰሳ ጥናት በአቶ ንጋቱ መኮንን ፣ በዶ/ር አመንሲሳ ከበደ እና በአቶ ፍቅሩ ንጉሴ አማካኝነት ጥናቱ እየቀረበ ይገኛል ።