በ2020 የቶኪዮ ኦሊምፒክ ለመሳተፍ ቅድመ ዝግጅት የሚካሄድበት ወቅት በመሆኑ ንፁህ ስፖርተኞችን ይዞ በውድድሩ ላይ ለመሰለፍ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶት ሲሰራ መቆየቱን ተገለፀ ፡፡
ይህው የተገለፀው የ2020 የቶኪዮ ኦሊምፒክ ዝግጅት እና የፀረ-ዶፒንግ እንቅስቃሴ በተመለከተ የኢትዮጵያ ብሔራዊ የፀረ-አበረታች ቅመሞች ጽ/ቤት/ETH-NADO/ ዋና ዳይሬክተር ክብር አቶ መኮነን ይደርሳል ባስተላለፉት ምልክት ነው፡፡
በ2013 በጀት ዓመት በተለይም ቀደም ሲል ከነበረው በተለየ መልኩ በዚህ ውድድር ላይ ለመሳተፍ በአለም አቀፉ የምርመራ ኤጀንሲ ቴክኒካል ቡድን (International Testing Agency Technical Group) ዝርዝር መስፈርቶች (Recommendations) የተቀመጡ በመሆናቸው በአገራችን ኢትዮጵያም እነዚህን መስፈርቶች መሰረት በማድረግ በርካታ እንቅስቃሴዎች ሲካሄዱ መቆየታቸዉን፤በዋናነትም በአገር አቀፍ ደረጃ የምርመራና ቁጥጥር ስራውን በልዩ ሁኔታ በማቀድ፣ አስፈላጊ ግብዓቶችን አስቀድሞ በማሟላት እና በሰው ኃይልና በበጀትም ጭምር በቂ ቅድመ ዝግጅቶችን በማድረግ ከሐምሌ ወር 2013 ዓ.ም ጀምሮ ላለፉት ጊዜያት የኢትዮጵያ ሻምፒዮናንና ሌሎችንም ማጣሪዎች ጨምሮ በውድድር ጊዜ (In Competition) እና ከውድድር ጊዜ ውጭ (Out of Competition) ሰፊ ምርመራና ቁጥጥር መካሂዷቸውን ዋና ዳይሬክተሩ ጨምረዉ አስታዉቀዋል፡፡
አቶ መኮነን ይደርሳል በማያያዝም እ.ኤ.አ ከጥር 2021 ጀምሮ ደግሞ የአለም አቀፉ የምርመራ ኤጀንሲ የቶኪዮ ኦሊምፒክ ቴክኒካል ቡድን (International Testing Agency Technical Group) ለአገራችን ያስቀመጠውን መስፈርት (Recommendation) መነሻ በማድረግ በአትሌቲክስ፣ በብስክሌት፣ በወርልድ ቴኳንዶ እና በውኃ ዋና ስፖርቶች ከ125 በላይ አትሌቶችን በምርመራ ቋት ውስጥ በማካተት ከስድስት ወራት በላይ ለሆነ ጊዜ በተከታታይ ጥብቅ የሆነ ከውድድር ጊዜ ውጭ ምርመራ (Out of Competition Testing) እና ቁጥጥር ተካሂዷል፡፡ በዚህም ለእያንዳንዱ አትሌት በስልጠና ቦታዎች፣ በመኖሪያ ቤት፣ በማሰልጠኛ ካምፕ(ሆቴል) … ወዘተ ከ600 በላይ ምርመራዎች መደረጋቸዉን፤የአትሌት ባዮሎጂካል ፓስፖርት(ABP)ፕሮግራምም በተጠናከረ መልኩ በመፈፀም ላይ መሆኑን አስረደድተዋል፡፡ይህም ካለፈው የአገራችን ነባራዊ ሁኔታ ጋር ሲነፃፀር እጅግ ከፍተኛ ስኬት ተደርጎ እደሚወሰድ አስታወቀዋል፡፡
በተጨማሪም በብሄራዊ ቡድኑ ውስጥ ለተካተቱ አትሌቶችና የስልጠና ቡድን አባላት በተለያዩ ጊዜያት መሰረታዊ የሆኑ የግንዛቤ ማስጨበጫ የስልጠና መድረኮች የተዘጋጁ ሲሆን በአለም አቀፉ ስታንዳርድ መሰረትም የE-Learning Platform በመዘርጋት ለእያንዳንዱ አትሌት ተደራሽ ለማድረግ የADEL ፕሮግራም ተግባራዊ በመደረግ ላይ ይገኛል፡፡ እያንዳንዱ አትሌትም የOn-line ስልጠናውን ትኩረት ሰጥቶ በመከታተል ያጠናቅቃል ተብሎ ይጠበቃል ብለዋል፡፡
በተያያዘ ሁኔታም ሌሎችም ከ2020 የቶኪዮ ኦሊምፒክ ቅድመ ዝግጅት ጋር የተያያዙ አስተዳደራዊ ተግባራትና አለም አቀፍ ግንኙነቱን የማጠናከር እንቅስቃሴዎች ትኩረት ተሰጥቷቸው እየተከናወኑ ሲሆን አገር አቀፍ የስፖርት ማህበራትን ጨምሮ ሁሉም ጉዳዩ የሚመለከታው ባለድርሻ አካላትም የተሰጣቸውን አለም አቀፍ ግዴታ (Recommendations) ለመወጣት እስከ ውድድሩ መጀመር ድረስ የበኩላቸውን ሚና ይወጣሉ ተብሎ እደሚጠበቅ ዋና ዳይሬክተሩ አስታዉቀዋል፡፡ ለዚህም ከእያንዳንዱ አለም አቀፍ የስፖርት ማህበር (International Federation) ጋር ያላቸውን ግንኙነት ማጎልበትና የስፖርት አበረታች ቅመሞችን ወይም ዶፒንግን በሚመለከት በተናጠል የሚቀመጡትን አቅጣጫዎች ተከታትሎ መፈፀም እንዲሁም በየስፖርት አይነቱ ያሉትን የፀረ-ዶፒንግ ህጎች በአግባቡ በመገንዘብ ተግባራዊ ማድረግ እደሚያስፈልግ አሳስበዋል፡፡
በመሆኑም በየደረጃው የተዘረጋውን ቅንጅታዊ አሰራር የበለጠ በማጠናከር ለቶኪዮ ኦሊምፒክ የሚደረገው እንቅስቃሴ የበለጠ ውጤታማ መሆን እንዲችል ፅ/ቤታችን ጥሪውን ያስተላልፋል በማለት ዋና ዳይሬክተሩ ገልፀዋል ፡፡
              የስፖርት አበረታች ቅመሞችን ወይም ዶፒንግን በጋራ እንቅከላከል !!!

By Ermias

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *