ሁሉም ጉዳዩ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት የስፖርት አበረታች ቅመሞችን በመከላከልና በመቆጣጠር ረገድ በባለቤትነት ስሜት መንቀሳቀስ እንደሚጠበቅባቸው ተገለፀ፤ 2ኛው ዙር የፀረ-አበረታች ቅመሞች ወይም ፀረ-ዶፒንግ የባለድርሻ አካላት ጉባኤ በጁፒተር ሆቴል ተካሂዷል፡፡
ETH-NADO has organized the 2nd edition stakeholders’ annual meeting. The meeting was held at Jupiter Hotel in Addis Ababa.
መስከረም 13/2012
በአገራችን የስፖርት አበረታች ቅመሞችን ወይም ዶፒንግን በዘላቂነት በመከላከልና በመቆጣጠር ፍትኃዊ የሆነ የውድድር ስርዓት ለመዘርጋት እና በአለም አቀፍ የውድድር መድረኮች የአገራችንን ውጤታማነት ለማጎልበት እንዲሁም ጤናማ ዜጎችን ለማፍራት የኢፌዲሪ መንግስት ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ በመስራት ላይ መሆኑ ይታወቃል፡፡ አገር አቀፍ ፌዴሬሽኖችን ጨምሮ ጉዳዩ የሚመለከታው አካላትም የበኩላቸውን ድርሻ በመወጣት ላይ ይገኛሉ፡፡
ስለሆነም በ2011 በጀት ዓመት በአገር አቀፍ ደረጃ የነበረውን አጠቃላይ የፀረ-ዶፒንግ እንቅስቃሴ በአግባቡ ለመገምገምና በተለያዩ ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ለመምከርና ቀጣይ አቅጣጫዎችን ለማስቀመጥ 2ኛው ዙር የበላድርሻ አካላት ጉባዔ ተካሂዷል፡፡ በዚህ ጉባኤ ላይ ብሄራዊ ፌዴሬሽኖችን ጨምሮጨምሮ ከ110 በላይ የሚሆኑ የተለያዩ መንግስታዊ ተቋማት፣ የሙያ ማህበራትና ሌሎችም አካላት ተወካዮች የተሳተፉ ሲሆን የ2011 በጀት ዓመት አጠቃላይ እንቅስቃሴና የእቅድ አፈፃፀም ሪፖርት፣ የብሄራዊ ፌዴሬሽኖች ተሞክሮ(የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን፣ የኢትዮጵያ ብስክሌት ፌዴሬሽንና የኢትዮጵያ ክብደት ማንሳት ፌዴሬሽን የስራ እንቅስቃሴና ተሞክሮዎች)፤ የጥናትና ምርምር ውጤቶች እና የባለድርሻ አካላት የፓርትነርሽፕ ፕሮግራም ረቂቅ ሰነድ ቀርቦ ሰፊ ውይይት ተደርጎበታል፡፡
በውይይቱ ላይም በአገር አቀፍ ደረጃ እየተካሄደ ያለው አጠቃላይ የፀረ-ዶፒንግ እንቅስቃሴ አበረታች እንደሆነና በአጭር ጊዜ ለሌሎች አገሮችና የስፖርት ተቋማትም ተሞክሮ ሊሆን የሚችሉ በርካታ መልካም ውጤቶችን ማስመዝገብ እንደተቻለ ተመላክቷል፡፡ በቀጣይ በ2012 በጀት ዓመት ላይ ትኩረት ተሰጥቷቸው ሊፈፀሙ የሚገባቸው ክፍተቶችም በውይይቱ ላይ ተነስተዋል፡፡
በተለይም አገር አቀፍ ፌዴሬሽኖች ከአለም አቀፍ ፌዴሬሽኖች ጋር በመናበብ የሚጠበቅባቸውን ግዴታ በአግባቡ መወጣት እንደሚገባቸው የተጠቆመ ሲሆን ሌሎች ባለድርሻ አካላትም የጉዳዩን አሳሳቢነት በመረዳት በባለቤትነት ስሜት መንቀሳቀስና የሚጠበቅባቸውን ገንቢ አስተዋፅኦ ማበርከት ይገባቸዋል ተብሏል፡፡