ጥቅምት 14/2011 ዓ.ም
በ47ኛው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና እና በአለም አቀፍ የማራቶን ውድድሮች ላይ የተከለከሉ የስፖርት አበረታች ቅመሞችን ወይም ዶፒንግን በመጠቀም የህግ ጥሰት በፈፀሙ አትሌቶች ላይ ከ4-8 ዓመት የሚደርስ ቅጣት ተጣለ፡፡
አትሌት ጫልቱ ሹምየ ረጋሳ ከሚያዝያ 09-14/2010 ዓ.ም በተካሄደው በ47ኛው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ በ800 ሜትር ውድድር ላይ የተሳተፈች ሲሆን ርቀቱን በ1 ደቂቃ ከ59 ሰከንድ ከ99 ማይክሮ ሰከንድ ሮጣ በማጠናቀቅና የሻምፒዮናውን ሪከርድ ጭምር በማሻሻል አሸናፊ መሆን ችላለች፡፡
ይሁን እንጅ የኢትዮጵያ ብሄራዊ የፀረ-አበረታች ቅመሞች ፅ/ቤት በዚህ ውድድር ላይ ባደረገው ምርመራ አትሌት ጫልቱ ሹምየ ረጋሳ ቴስቴስትሮን (Exogenous Origin of Testosterone and 5aAdiol) የተባለውን የተከለከለ መድኃኒት መጠቀሟ ተረጋግጧል፡፡ ስለሆነም ጉዳዩን በማጣራት አትሌቷ እ.ኤ.አ ከመስከረም 06/2018 ዓ.ም ጀምሮ እስከ መስከረም 06/2022 ድረስ ለተከታታይ አራት ዓመታት በማንኛውም አገር አቀፍም ይሁን አለም አቀፍ ውድድር ላይ እንዳትሳተፍ እንዲሁም በውድድሩ ላይ ያስመዘገበቸው ውጤት እንዲሰረዝና የተሰጣትንም የገንዘብና የሜዳሊያ ሽልማት ለፌዴሬሽኑ እንድትመልስ ቅጣት ተላልፏል፡፡
በተመሳሳይ መልኩ አትሌት ብርቱካን አደባ በሪሁን ቀደም ሲል እ.ኤ.አ ህዳር 13/2016 በተካሄደው የሻንጋይ ኢንተርናሽናል ማራቶን ላይ በምትወዳደርበት ወቅት የተከለከለ መድኃኒት ተጠቅማ በመገኘቷ የአራት ዓመት እገዳ የተጣለባት መሆኑ ይታወቃል፡፡ ይሁን እንጂ አትሌቷ ጉዳዩን ለማጣራት የተሰጣትን ጊዜያዊ እገዳ በመጣስ እ.ኤ.አ ጥር 19/2018 በተካሄደው የሙስካት ማራቶን ላይ መሳተፏ የተረጋገጠ ሲሆን በዚህ ውድድር ላይም በተደረገላት ምርመራ Prednisolone የተባለውን የተከለከለ መድኃኒት በድጋሜ መጠቀሟን ማወቅ ተችሏል፡፡ በመሆኑም አትሌቷ ቀደም ሲል በፈፀመችው የህግ ጥሰት የተጣለባትን ጊዜያዊ እገዳ በመተላለፍ በሙስካት ማራቶን ላይ በመሳተፏ እንዲሁም ለሁለተኛ ጊዜ የተከለከለ መድኃኒት መጠቀሟ በመረጋገጡ ከአሁን በፊት ከተጣለባት ቅጣት በተጨማሪ እ.ኤ.ኤ እስከ ሰኔ 22/2029 ድረስ ለተከታታይ ስምንት ዓመታት በምንም አይነት ስፖርታዊ ውድድር ላይ እንዳትሳተፍና ያስመዘገበቻቸው ውጤቶች እንዲሰረዙ ቅጣት ተላልፎባታል፡፡
የኢትዮጵያ ብሄራዊ የፀረ-አበረታች ቅመሞች ፅ/ቤት በአገራችን ንፁህ ስፖርት እንዲስፋፋ በማድረግ በትክክለኛው መንገድ ተወዳድረው የሚያሸንፉ ንፁኃን ስፖርተኞች እንዲፈሩ ምቹ ሁኔታ የመፍጠር ዓላማን በመያዝ ቀደም ሲል ጀምሮ ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ የተሸጋገረ መሆኑ ይታወቃል፡፡ በዚህም መሰረት ፅ/ቤቱ በሚኒስትሮች ም/ቤት ደንብ ቁጥር 400/2009 የተሰጡትን ተግባርና ኃላፊነቶች በአለም አቀፍ የፀረ-ዶፒንግ ህጎችና ስታንዳርዶች መሰረት ነፃና ገለልተኛ ሆኖ በመፈፀም ላይ የሚገኝ መሆኑ የሚታወቅ ሲሆን በተለይም በየደረጃው ያለውን ግንዛቤ የማጎልበት፣ የምርመራና ቁጥጥር ተግባራትን እንዲሁም የተለያዩ የአሰራር ስርዓቶችን የማዘጋጀትና ተግባራዊ የማድረግ እና የመሳሰሉትን እንቅስቃሴዎች ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ እያከናወነ ነው፡፡
ከዚህም ጋር ተያይዞ ቀደም ሲል በተለያዩ ውድድሮች ላይ የተከለከሉ የስፖርት አበረታች ቅመሞችን ተጠቅመው በተገኙ አትሌቶችና በዚህ ህገ-ወጥ ተግባር ውስጥ በተሳተፉ ፋርማሲዎች ላይ የእርምት እርምጃ እንዲወሰድ ማድረጉ ይታወሳል፡፡
በቀጣይም እነዚህ ተግባራት ተጠናክረው የሚቀጥሉ መሆኑን እየገለፅን በተለይም በተለያዩ አለም አቀፍ የማራቶን ውድድሮች ላይ በግላቸው በማናጀርም ይሁን በሌላ መንገድ ተመዝግበው የሚሳተፉ አትሌቶች በየጊዜው ጥብቅ ክትትልና ቁጥጥር እንደሚደረግ በመገንዘብ አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ፅ/ቤታችን ጥሪውን ያስተላልፋል፡፡