ታዳጊ ወጣቶች በስፖርት አበረታች ቅመሞች ወይም ዶፒንግ ዙሪያ ያላቸውን ግንዛቤ ለማጎልበት የOutreaching ፕሮግራም በአርባ ምንጭ ከተማ በመካሄድ ላይ ነው፡፡
ቀን፡- ነሐሴ 17/2011 ዓ.ም
በአገራችን ከ51,000 በላይ ታዳጊ ወጣቶች የሚሳተፉበት የስፖርት ስልጠና ፕሮጀክት ተዘርግቶ ቀደም ሲል ጀምሮ ተግባራዊ በመደረግ ላይ መሆኑ የሚታወቅ ሲሆን እነዚህ ታዳጊዎች በቀጣይ በየደረጃው በስፖርቱ ውስጥ ብቁ ተወዳዳሪ በመሆን አገራችንንም በተለያዩ አለም አቀፍ ውድድሮች እንደሚወክሉ ይታመናል፡፡
ስለሆነም ከስፖርት ስልጠናው ጎን ለጎን በአበረታች ቅመሞች ወይም ዶፒንግ ዙሪያ መሰረታዊ ግንዛቤ መጨበጥ እና እውቀት መያዝ የሚኖርባቸው በመሆኑ የኢትዮጵያ ብሄራዊ የፀረ-አበረታች ቅመሞች ፅ/ቤት (ETH-NADO) አርባ ምንጭ ከተማ በሚካሄደው የታዳጊ ወጣቶች የምዘና ውድድር ላይ የOutreaching ፕሮግራም በማካሄድ ላይ ይገኛል፡፡
በዚህ የOutreaching ፕሮግራም ላይ አካል ጉዳተኞችን ጨምሮ ታዳጊ ስፖርተኞችና የስፖርት ባለሞያዎች እንዲሁም የስፖርቱ ማህበረሰብ በስፋት በመሳተፍ ላይ የሚገኙ ሲሆን ከላይ እንደተገለፀው በተለይም ታዳጊ ወጣቶች በስፖርት አበረታች ቅመሞች ወይም ዶፒንግ ዙሪያ በቂ ግንዛቤ እንደሚጨብጡ ይጠበቃል፡፡ ሰፊ የሆነ የስፖርቱ ማህበረሰብ ንቅናቄም በመካሄድ ላይ ይገኛል፡፡