የተለያዩ የስፖርት ባለሞያዎችን ያቀፈ ቋሚ የፀረ-ዶፒንግ ፈሮም ተቋቋመ፤ ፎረሙ በየስድስት ወሩ መደበኛ የውይይት መድረክ ይኖረዋል፡፡

የካቲት 22/2011 ዓ.ም

የስፖርት አበረታች ቅመሞች ወይም ዶፒንግ የአገራችን ስፖርት በተለይም የአትሌቲክሱ ተግዳሮት መሆን ከጀመረ ውሎ አድሯል፡፡ ከዚህም ጋር ተየይዞ ችግሩን በዘላቂነት ለመከላከልና ለመቆጣጠር በመንግስትና በተለያዩ ባለድርሻ አካላት በኩለት ቀደም ሲል ጀምሮ ዘርፈ ብዙ ጥረቶች ሲደረጉ የቆዩ ሲሆን አበረታች ውጤቶችም በመመዝገብ ላይ መሆናቸው ይታወቃል፡፡

ስለሆነም እነዚህን ጅምር እንቅስቃሴዎች የበለጠ በማጠናከር ንፁህ ስፖርትን ማስፋፋት እና በአለም አቀፍ መድረኮች የተገነባውን የአገራችንን መልካም ገፅታ ማስቀጠል የሚጠበቅ ሲሆን ለዚህም ጉዳዩ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በባለቤትነት እና በኃላፊነት ስሜት እንዲሳተፉ ማድረግ ይገባል፡፡ ከዚህም ጋር ተያይዞ በተለያዩ ስፖርቶች በብሄራዊ ቡድን፣ በክለብ ግላቸው በአልጣኝነት፣ በዳኝነት፣ በአትሌት ማናጀርነት እና በመሳሰሉት የስፖርት የስራ ዘርፎች ተሰማርተው እያገለገሉ ያሉ የስፖርት ባለሞያዎችን ያቀፈ የስፖርት ባለሞያዎች ቋሚ የፀረ-ዶፒንግ ፎረም በዛሬው እለት በኢትዮጵያ ሆቴል እንዲቋቋም እና የመጀመሪያ ጉባኤው እንዲካሄድ ተደርጓል፡፡

ፎረሙ በዋናነት የስፖርት ባለሙያዎች በአገራችን በሚካሄደው የፀረ-አበረታች ቅመሞች እንቅስቃሴ ውስጥ በባለቤትነት እና በኃላፊነት የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ የማስቻል አላማ ያለው ሲሆን በየጊዜው በሚካሄደው መደበኛ ጉባኤው አጠቃላይ አገራዊ እንቅስቃሴውን በጋራ መገምገም፣ ቀጣይ አቅጣጫዎችን ማስቀመጥና በቅንጅት እንዲፈፀሙ እንዲሁም በባለሞያዎች መካከል የተሻሉ ተሞክሮዎችን በመቀመር ከአንዱ ወደ ሌላው ለማስፋት ያስችላል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

በዚህም መሰረት የቋሚ ፎረሙ የራሱ የአሰራር ስርዓት የተዘረጋለት ሲሆን በየስድስት ወሩ ቋሚ የውይይት መድረክም ያካሂዳል፡፡ በውይይቱ ላይም አገራዊ የፀረ-ዶፒንግ እቅዶች፣ የአፈፃፀም ሪፖርቶች፣ የጥናትና ምርምር ውጤቶች፣ ወቅታዊ ጉዳዮች እና የስፖርት አበረታች ቅመሞችን የሚመለከቱ የተለያዩ ወቅታዊ አጀንዳዎች እየቀረቡ ውይይት ይደረግባቸዋል፡፡ ቀጣይ አቅጣጫዎችም በጋራ እየተቀመጡ ወደ ትግበራ ይሸጋገራሉ፡፡

በፎረሙ የምስረታ ጉባኤ ላይ የተገኙት እና የመክፈቻ ንግግር ያሰሙት የኢፌዲሪ ስፖርት ኮሚሽን ም/ኮሚሽነር ክቡር አቶ ጌታቸው ባልቻ የኢፌዲሪ መንግስት ይህን ችግር በዘላቂነት ለመከላከልና ለመቆጣጠር እስካሁን ሰፊ ትኩረት ሰጥቶ ሲንቀሳቀስ መቆየቱን ገልፀው በቀጣይም ስፖርቱን የመታደግ ስራ በዚሁ አግባብ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልና ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ገንቢ ሚና መወጣት እንደሚገባቸው ጠቁመዋል፡፡

በተመሳሳይ መልኩ የኢትዮጵያ ብሄራዊ የፀረ-አበረታች ቅመሞች ፅ/ቤት የቦርድ ሰብሳቢ ክቡር ፕሮፌሰር አክሊሉ አዛዥ አርሶ አደር ሰብሉን ከአረምና ከመጤ ትል እንሚጠብቀው ሁሉ የስፖርት ባለሞያዎችም ስፖርተኞቻቸውን ከአበረታች ቅመሞች ወይም ዶፒንግ ሊጠብቁ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *