የአለም አቀፉ የፀረ-ዶፒንግ ኤጀንሲ(WADA) ነፃና ገለልተኛ የኦዲት ኮሚቴ በማቋቋም የኢትዮጵያ ብሄራዊ የፀረ-አበረታች ቅመሞች ፅ/ቤትን እና የአገራችንን አጠቃላይ የፀረ-ዶፒንግ እንቅስቃሴ በጥልቀት በመገምገምና ኦዲት በማድረግ ላይ ነው፡፡
ቀን፡- ሚያዝያ 24/2011 ዓ.ም
የኢትዮጵያ ብሄራዊ የፀረ-አበረታች ቅመሞች ፅ/ቤት (ETH-NADO) የአለም አቀፉን የፀረ-ዶፒንግ ህግ (World Anti-Doping Code) እና የአገራችንን ህጎች መሰረት ባደረገ መልኩ በሚኒስትሮች ም/ቤት ደንብ ቁጥር 400/2009 ቀደም ሲል ተቋቁሞ ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ የተሸጋገረ መሆኑ ይታወቃል፡፡ በዚህም መሰረት ፅ/ቤቱ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር በቅንጅት ባደረገው ዘርፈ ብዙ እንቅስቃሴ አገራችን ኢትዮጵያ ከገባችበት የእገዳ ስጋት ወጥታ ዶፒንግን በመከላከልና በመቆጣጠር ረገድ ለሌሎችም አገሮች ተሞክሮ ሊሆኑ የሚችሉ አበረታች ተግባራትን ማከናወን ተችሏል፡፡
በተለይም የፅ/ቤቱን ተቋማዊ አቅም ከመገንባት ጀምሮ በየደረጃው የትምህርትና ስልጠና፣ የምርመራና ቁጥጥር፣ የህግ ጥሰቶች ሲፈፀሙ ተከታትሎ አስፈላጊው እርምጃ እንዲወሰድ የማድረግ እና ሌሎችም የፀረ-ዶፒንግ እንቅስቃሴዎች ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቷቸው ሲከናወኑ ቆይተዋል፡፡ በዚህም በአለም አቀፍ የፀረ-ዶፒንግ ተቋማትና የስፖርት ማህበራት ሳይቀር እውቅና የተሰጣቸውን ውጤቶች ማስመዝገብ ተችሏል፡፡
ስለሆነም እነዚህ ተግባራት በአለም አቀፉ የፀረ-ዶፒንግ ህግ (World Anti-Doping Code)፣ በተለያዩ አለም አቀፍ ስታንዳርዶች (International Standards) እና የአሰራር ስርዓቶች መሰረት መፈፀማቸውን ለማረጋገጥ በአለም አቀፉ የፀረ-ዶፒንግ ኤጀንሲ (WADA) ነፃና ገለልተኛ የሆነ የኦዲት ቡድን ተቋቁሞ ከሚያዝያ 24/2011 ዓ.ም ጀምሮ ወደ አገራችን በመምጣት በጥልቀት በመገምግምና በመፈተሸ ላይ ይገኛል፡፡ ይህ የኦዲት ቡድን ከአለም አቀፉ የፀረ-ዶፒንግ ኤጀንሲ (WADA)፣ ከኖርዌ እና ከሮማንያ የተወጣጡና በዘርፉ የካበተ ልምድ ያላቸውን የስራ ኃላፊዎች የያዘ ሲሆን ግምገማው በነገው እለትም የሚቀጥል ይሆናል፡፡
ግምገማው ጥልቀት ባለው መልኩ የሚካሄድ ሲሆን የፅ/ቤቱ አደረጃጀትና አጠቃላይ አሰራር እንዲሁም የሰው ኃይል ስምሪት፣ ትምህርትና ስልጠና፣ የተለያዩ የዶፒንግ ምርመራና ቁጥጥር ተግባራት፣ የህግ ጥሰት የሚፈፅሙ አካላትን በማጣራት የሚወሰደው እርምጃ አፈፃፀም፣ የኢንተለጀንስና ኢንቨስቲጌሽን ተግባራት እና የመሳሰሉት ጉዳዮች በአለም አቀፍ ህጎችና ስታንዳርዶች መሰረት መፈፀም አለመፈፀማቸውን በማስረጃ በማስደገፍና የፅ/ቤቱን ሰነዶችን በመፈተሽ የመመርመር ስራ በመከናወን ላይ ይገኛል፡፡
የኦዲት ቡድኑ የፅሁፍ ግብረ-መልስም በአጭር ጊዜ ለኢትዮጵያ ብሄራዊ የፀረ-አበረታች ቅመሞች ፅ/ቤት ይላካል ተብሎ ይጠበቃል፡፡