የኢትዮጵያ ብሄራዊ የፀረ-አበረታች ቅመሞች ፅ/ቤት የተከለከለ መድኃኒት በመጠቀም የህግ ጥሰት በፈፀሙ አትሌቶች ላይ የቅጣት ውሳኔ አስተላልፏል፡፡
ፅ/ቤቱ አበረታች ቅመሞችን ወይም ዶፒንግን በመከላከልና በመቆጣጠር ፍትኃዊ የውድድር ስርዓት እንዲኖር ለማድረግና በአለም አቀፍ የውድድር መድረኮችም ንፁህ በሆነ መንገድ ተወዳድረው የሚያሸንፉ ጤናማና ውጤታማ የሆኑ አትሌቶች እንዲፈሩ ለማስቻል የህግ ማዕቀፎችን በማውጣት ተግበራዊ ማድረግን፣ ወጥ የአሰራር ስርዓት መዘርጋትን፣ ትምህርና ስልጠናን፣ ምርመራ ቁጥጥርን፣ የተለያዩ የኢንተለጀንስና ኢንቨስቲጌሽን ተግባራትን እና የፅ/ቤቱን የማስፈፀም አቅም መገንባትን ጨምሮ በየደረጀው የተለያዩ አበረታች እንቅስቃሴዎችን በማካሄድ ላይ ሲሆን በተለያዩ አለም አቀፍ ውድድሮች ላይ በተደረጉ ምርመራዎች የተከለከሉ መድኃኒቶችን ተጠቅመው በተገኙ አትሌቶች ላይ ጊዜያዊ እገዳዎችን በማስተላለፍ ማጣሪያዎችን ሲያደርግ ቆይቷል፡፡
ከዚህም ጋር በተያያዘ ከዚሀ በታች ስማቸዉ በተዘረዘሩት አትሌቶች ላይ ጊዜያዊ እገዳው ከተላለፈበት ጊዜ ጀምሮ ለተከታታይ 4 (አራት) ዓመታት በአገር አቀፍ፣ በአለም አቀፍና በሌሎችም ማናቸውም ስፖርታዊ ውድድሮች ላይ እንዳይሳተፉ ቅጣት ተጥሎባቸዋል፡፡
- አትሌት ብርቱካን አደባ በሪሁን
ምርመራ የተደረገበት ውድድር:- Shanghai International Marathon የተጠቀሙት የተከለከ አበረታች መድኃኒት :- Exogenous Steroid
ምርመራ የተደረገበት ቀን:- እ.ኤ.አ ህዳር 13 /2016
ቅጣት:- 4 ዓመት እ.ኤ.አ ከሰኔ 22/ 2017 – ሰኔ 22/2021 - አትሌት እዮብ አለሙ ወ/ጊዮርጊስ
ምርመራ የተደረገበት ውድድር:- China Longkou International Marathon
የተጠቀሙት የተከለከ አበረታች መድኃኒት:- EPO (Erythropoietin)
ምርመራ የተደረገበት ቀን:- እ.ኤ.አ ጥቅምት 29/2017
ቅጣት:- 4 ዓመት እ.ኤ.አ ከየካቲት 05/2018 – የካቲት 05/2022
የኢትዮጵያ ብሄራዊ የፀረ-አበረታች ቅመሞች ፅ/ቤት በቀጣይም የተጀመረውን እንቅስቃሴ አጠናክሮ የሚቀጥል ሲሆን በተለይም በየደረጃው የኢንተለጀንስና ኢንቨስትጌሽን ተግባራትን ጨምሮ የምርመራና ቁጥጥር ተግባራትን በማከናወን የህግ ጥሰት በሚፈፅሙ አካላት ላይ አስተማሪ የሆኑ እርምጃዎችን የሚወሰድ መሆኑን እንገልፃለን፡፡ ሁሉም ባለድርሻ አካላትም በዚህ እንቅስቃሴ ውስጥ የበኩላቸውን ገንቢ አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡