አትሌት አበሰኒ ዳባ ጨመዳ የተከለከለ የስፖርት አበረታች ቅመም መጠቀሟ በመረጋገጡ ለ4 (አራት) ተከታታይ ዓመታት እገዳ ተላልፎባታል፡፡
ህዳር 28/2011 ዓ.ም
የኢትዮጵያ ብሄራዊ የፀረ-አበረታች ቅመሞች ፅ/ቤት በአገራችን በየደረጃው ጠንካራ ምርመራና ቁጥጥር በማድረግ ንፁህ ስፖርት እንዲስፋፋ እና ጤናማ የሆኑ ተተኪ ስፖርተኞች እንዲፈሩ ለማስቻል ቀደም ሲል ጀምሮ የተለያዩ አበረታች ተግባራትን እያከናወነ መሆኑ የሚታወቅ ሲሆን በተለይም በተለያየ መንገድ የህግ ጥሰቶችን የሚፈፅሙ አካላትን በመከታተልና በማጣራት የማስተካከያ እርምጃዎች እንዲወሰዱ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡
በዚህም መሰረት የተከለከሉ የስፖርት አበረታች ቅመሞችን በመጠቀም የህግ ጥሰት የፈፀሙ አትሌቶች እና በተለያየ መንገድ በህግ ጥሰቶች ውስጥ የተሳተፉ አካላትን በመለየት በተለይም በፋርማሲዎችና በመድኃኒት አቅራቢ ድርጅቶች እና ግለሰቦች ላይ የተለያዩ አስተዳደራዊ እርምጃዎች መወሰዳቸው ይታወሳል፡፡
በተመሳሳይ መልኩ አትሌት አብሰኒ ዳባ ጨሜዳ እ.ኤ.አ ህዳር 05/2017 ቻይና በተካሄደው የፒዥው (Pizhou) ግማሽ ማራቶን ላይ በተከለከሉ የስፖርት ፀረ-አበረታች ቅመሞች ዝርዝር S3, Beta-2 Agonists ስር የሚገኘውንና Higenamine የተባለውን የተከለከለ ንጥረ-ነገር ተጠቅማ መገኘቷ የተረጋገጠ ሲሆን ጉዳዩን በማጣራት አትሌቷ ጊዜያዊ እገዳ ከተጣለባት እ.ኤ.አ ነሐሴ 06/2018 ጀምሮ እስከ ነሐሴ 06/2022 ድረስ ለተከታታይ አራት ዓመታት በማንኛውም አገራዊ፣ አህጉር አቀፍና አለም አቀፍ የስፖርት ውድድሮቸ ላይ እንዳትሳተፍ እንዲሁም በወቅቱ ያስመዘገበችው ውጤት እንዲሰረዝ ቅጣት ተጥሎባታል፡፡
በአገራችን ችገሩን ከመሰረቱ ለመከላከልና ለመቆጣጠር የምርመራና ቁጥጥር ስራው በቀጣይነትም ወጥ በሆነ መልኩ ተጠናክሮ የሚቀጥል ሲሆን ፅ/ቤታችን ክለቦችን፣ የአትሌት ማናጀሮችንና ብሄራዊ ፌዴሬሽኖችን ጨምሮ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ገንቢ አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱ ጥሪውን ያስተላልፋል፡፡
በመጨረሻም እ.ኤ.አ በ2018 በጀት ዓመት ከ409 በላይ በውድድር ጊዜና ከውድድር ጊዜ ውጭ የስፖርተኞች ምርመራዎች የተካሄዱ መሆናቸውን እናሳውቃለን፡፡