የኢትዮጵያ ብሄራዊ የፀረ-አበረታች ቅመሞች እንቅስቃሴ ውጤታማ እና በአጭር ጊዜ ፈጣን ለውጦች የተመዘገቡበት እንደሆነ ተጠቆመ፤ የአለም አቀፉ የፀረ-ዶፒንግ ኤጀንሲ (WADA) የአገራችንን አፈፃፀም ገምግሟል፡፡
ህዳር 28/2011 ዓ.ም
የኢትዮጵያ ብሄራዊ የፀረ-አበረታች ቅመሞች ፅ/ቤት ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ በኢፌዲሪ መንግስት ተቋቁሞ ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ የተሸጋገረ መሆኑ የሚታወቅ ሲሆን አፈፃፀሙም በየዓመቱ ከአለም አቀፉ የፀረ-ዶፒንግ ኤጀንሲ (WADA) ጋር በሚካሄዱ የጋራ መድረኮች በጥልቀት ይገመገማል፡፡
ከዚህም ጋር ተያይዞ በየደረጃው የስፖርት አበረታች ቅመሞችን ወይም ዶፒንግን በመከላከልና በመቆጣጠር ረገድ እ.ኤ.አ በ2018 በጀት ዓመት በአገራችን የተካሄደው አጠቃላይ እንቅስቃሴ ከህዳር 26-27/2011 ዓ.ም የአለም አቀፉ የፀረ-ዶፒንግ ኤጀንሲ (WADA) የስራ ኃላፊዎች በተገኙበት ተገምግሟል፡፡ በተለይም ባለፉት ጊዜያት ፅ/ቤቱን በሰው ኃይልና በግብዓት ከማደራጀት ጀምሮ የትምህርትና ስልጠና፣ የምርመራና ቁጥጥር፣ የተለያዩ የአሰራር ስርዓቶችን የመዘርጋትና የመተግበር፣ አለም አቀፍ ግንኙነቱን የማጠናከር እና የመሳሰሉት በርካታ ተግባራት የተከናወኑ ሲሆን ዝርዝር አፈፃፀማቸውም ቀርቦ ሰፊ ውይይት ተካሂዶባቸዋል፡፡
የቀረበውን ሪፖርት መነሻ በማድረግ በተደረገው ውይይት ላይም ፅ/ቤቱ በአጭር ጊዜ ፈጣን ለውጦችን ማስመዝገብ እንደቻለ እና በተለይም በአትሌቲክስ ስፖርት ውጤታማ ተግባራት መፈፀማቸው ተገልጧል፡፡ ይህም ለሌሎች የአፍሪካ አገሮችም በምሳሌነት የሚጠቀስ መሆኑንና ተሞክሮውንም ማስፋት እንደሚገባ የስራ ኃላፊዎቹ ጠቁመዋል፡፡
በአገራችን በዚህ መልኩ የተጀመረው እንቅስቃሴ በቀጣይም ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ያሳሰቡት የአለም አቀፉ የፀረ-ዶፒንግ ኤጀንሲ የስራ ኃላፊዎች ሁሉም ባለድርሻ አካላት የጋራ ርብርብ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው የገለፁ ሲሆን በተለይም አገራችን ኢትዮጵያ በቶኪዮ ኦሊምፒክና በሌሎችም አለም አቀፍ ውድድሮች ላይ ለሚኖራት ተሳትፎ ከአሁኑ ጀምሮ አስፈላጊው የአበረታች ቅመሞች ወይም ዶፒንግ ምርመራና ቁጥጥር ስራ መጀመር እንደሚገባ፣ አለም አቀፍ ህጎችንና ስታንዳርዶችን በየጊዜው በመከታተል በአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ተግባራዊ እንዲሆኑ ማድረግ እንደሚያስፈልግ፣ የስፖርት አበረታች ቅመሞችን የሚመለከቱ ጉዳዮች መደበኛ ትምህርቱን ጨምሮ በስፖርቱ የተለያዩ የስልጠና ካሪኩለሞች ውስጥ ተካቶ ተግባራዊ እንዲሆን ማድረግ እና የመሳሰሉትን ተግባራት ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ ማከናወን እንደሚገባ ምክረ-ኃሳቦችን አስቀምጠዋል፡፡
የስራ ኃላፊዎቹ የፅ/ቤቱን ቢሮም ጎብኝተዋል፡፡