የአትሌት ድርቤ ወልተጅ ጉዳይን በተመለከተ መግለጫ ስለመስጠት
መስከረም 2/2018 ዓ.ም
አዲስ አበባ
የኢትዮጵያ ፀረ-አበረታች ቅመሞች ባለስልጣን በህግ በተሰጠው ስልጣንና ኃላፊነት መሰረት በስፖርት ውድድር ወቅትና ከውድድር ጊዜ ውጭ የአበረታች ቅመሞች ወይም ዶፒንግ ምርመራ የሚያካሂድ መሆኑ ይታወቃል። በዚህም መሰረት የምርመራ እቅድ(TDP) በማዘጋጀት እ.ኤ.አ የካቲት 25/2025 ለአትሌት ድርቤ ወልተጅ ከውድድር ጊዜ ውጭ ምርመራ (Out of Competition Test) ለማካሄድ ሙከራ ያደረገ ሲሆን ሳይሳካ ቀርቷል። ምርመራውም የተደናቀፈው አትሌቷ ፍቃደኛ ሳትሆን በመቅረቷና በምርመራ ባለሞያዎች(Sample Collection Personnel) ላይ ጫና በመደረጉ ምክንያት እንደሆነ መገንዘብ ተችሏል።
ይህንንም መሰረት በማድረግ ጉዳዩን በጥልቀት በማጣራት ነፃና ገለልተኛ በሆነ የዳኝነት አካል (Hearing Panel) እንዲታይ የተደረገ ሲሆን ባለስልጣን መ/ቤቱ ያለውን መረጃና ማስረጃ በማቅረብ በአትሌቷ ላይ አግባብነት ያለው ህጋዊ እርምጃ እንዲወሰድ ተከራክሯል፡፡ ይሁን እንጅ የዳኝነት አካሉ ግራ ቀኙን ማለትም አትሌቷንና የኢትዮጵያ ፀረ-አበረታች ቅመሞች ባለስልጣንን በማከራከር በህግ አግባብ ትክክል ነው ብሎ ያመነበትን ውሳኔ ወስኗል፡፡ ባለስልጣን መ/ቤቱም እንደ ከሳሽ አካል በውሳኔው ደስተኛ ባይሆንም በአለም አቀፉ ህግ መሰረት ውሳኔውን በመቀበል ለአትሌቷ እንዲሁም ለአለም አቀፍ ተቋማት አሳውቋል፡፡
ከዚህም በመነሳት የአለም አትሌቲክስ የኢንተግሪቲ ዩኒት (AIU) ጉዳዩን በተለይም የቀረቡትን ሰነዶችና ሌሎችንም መረጃዎች በመመርመር ለአለም አቀፉ የስፖርት ግልግል ፍ/ቤት (CAS) ይግባኝ አቅርቧል፡፡ ከዚህም ጋር ተያይዞ የኢትዮጵያ ፀረ-አበረታች ቅመሞች ባለስልጣን በማንኛውም ደረጃ በሚፈፀሙ የፀረ-አበረታች ቅመሞች የህግ ጥሰት ላይ አስተማሪ የሆነ እርምጃ እንዲወሰድ ለማስቻል በትኩረት የሚሰራ መሆኑን እየገለፅን በአትሌት ድርቤ ወልተጅ ጉዳይ ላይም አግባብነት ያለው ፍትኃዊ ውሳኔ እንዲወሰን አስፈላጊውን ድጋፍና ያላሳለሰ ጥረት ሁሉ የሚያደርግ መሆኑን ያረጋግጣል፡፡
የኢትዮጵያ ፀረ-አበረታች ቅመሞች ባለስልጣን