1. የፀረ-አበረታች ቅመሞች ሕጉን ጨምሮ ከዓለም አቀፉ የፀረ-አበረታች ቅመሞች ኤጀንሲ ሕጎችና ደንቦች ጋር የተጣጣመ እና በየደረጃው ዶፒንግን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚያስችል ብሔራዊ የፀረ-አበረታች ቅመሞች ፖሊሲ እና የማስፈፀሚያ ስትራቴጅ በማዘጋጀት ተግባራዊ እንዲሆን ያደርጋል፤
  2. በየደረጃው ህብረተሰቡንና በተለይም ደግሞ የስፖርቱን ማህበረሰብ በዶፒንግ እና በስፖርቱ ውስጥ በሚያስከትላቸው ጉዳቶች ዙሪያ ለማስተማር የሚያስችሉ የተለያዩ የሥልጠናና የግንዛቤ መፍጠሪያ ፕሮግራሞችን ይቀርፃል፤ ተግባራዊ ያደርጋል፤
  3. በዓለም አቀፉ የፀረ-አበረታች ቅመሞች ኤጀንሲ በየጊዜው ማሻሻያ ተደርጎባቸው የሚወጡ የተለያዩ መመሪያዎች እና ዓለም አቀፍ ደረጃዎች ከአገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታ ጋር ተጣጥመው ተግባራዊ እንዲሆኑ ያደርጋል፤
  4. በአትሌቶች ላይ የዶፒንግ ምርመራዎችን ያካሂዳል፤
  5. የዶፒንግ ሕግን በሚጥሱ አትሌቶች እና የአትሌት ደጋፊ ሠራተኞች ላይ በዓለም አቀፉ የፀረ-አበረታች ቅመሞች ሕግ አንቀጽ 2፣ 10 እና 23.2.2 መሠረት ቅጣት ይጥላል፤
  6. በዓለም አቀፉ የፀረ-አበረታች ቅመሞች ሕግ እና በየጊዜው በዓለም አቀፉ የፀረ-አበረታች ቅመሞች ኤጀንሲ በሚወጡ እና ማሻሻያ በሚደረግባቸው የተለያዩ መመሪያዎች እና ዓለም አቀፍ ደረጃዎች መሠረት ለአትሌቶች፣ ለአትሌት ድጋፍ ሰጭ ሠራተኞች እንዲሁም ለዶፒንግ ቁጥጥር ባለሞያዎች ከናሙና አሰባሰብ ሂደት እና ምርመራ ጋር በተያያዘ ተከታታይ መረጃ ይሰጣል፤
  7. በዓለም አቀፉ የፀረ-አበረታች ቅመሞች ሕግ አንቀጽ 14.4 መሠረት የመንግስትንና የዓለም አቀፉን የፀረ-አበረታች ቅመሞች ኤጀንሲ ግዴታዎችን ለማሟላት ዓመታዊ የሥራ እንቅስቃሴውን በተመለከተ በየዓመቱ መረጃዎችን ይሰጣል፤
  8. የስፖርተኞች ጤናና ደህንነት በአግባቡ እንዲጠበቅ ለማድረግ በውድድርና መዝናኛ ስፖርቶች ላይ ከተከለከሉና በሰው ሰራሽ መንገድ የአካል ብቃትን ለማሻሻል ከሚዘጋጁና ከተከለከሉ የዶፒንግ ዘዴዎች የፀዳ ፍትኃዊ የውድድርና ተሳትፎ ሥርዓት እንዲኖር ያበረታታል፤
  9. በዓለም አቀፉ የፀረ-አበረታች ቅመሞች ሕግ አንቀጽ 2 መሠረት የአበረታች ቅመሞች የሕግ ጥሰት እንዳይፈፀም ይከላከላል፤
  10. በዓለም አቀፉ የፀረ-አበረታች ቅመሞች ሕግና በኢትዮጵያ የፀረ-አበረታች ቅመሞች መመሪያ መሠረት የአበረታች ቅመሞች የሕግ ጥሰቶች ጉዳይን የሚመለከት የውጤት አስተዳደር ኮሚቴ ያቋቁማል፤
  11. የዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (10) አጠቃላይ ድንጋጌ እንደተጠበቀ ሆኖ የውጤት አስተዳደር ኮሚቴው በኢትዮጵያ የፀረ-አበረታች ቅመሞች መመሪያ መሰረት ዶፒንግን በሚመለከቱ ጥፋቶች ዙሪያ የዲስፕሊን እርምጃዎችን ለመውሰድ የመጀመሪያ ደረጃ ውሳኔ ሰጭ አካል ሆኖ እንዲሰራ ይደረጋል፤
  12. በዓለም አቀፉ የፀረ-አበረታች ቅመሞች ሕግ አንቀጽ 4.4 መሠረት የተደነገገው የሥልጣን ገደብ እንደተጠበቀ ሆኖ የተከለከሉ አበረታች ቅመሞች ለህክምና አገልግሎት እንዲውሉ ለማድረግ የሚቀርቡ ጥያቄዎችን ገምግሞ የሚወስን የህክምና ንዑስ ኮሚቴ ያቋቁማል፣
  13. በስፖርት ውስጥ የሚፈጸሙ ከዶፒንግ ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ላይ ምርመራ ያደርጋል፤
  14. ከአህጉር እና ዓለም አቀፍ የፀረ-አበረታች ቅመሞች ተቋማት ጋር በቅንጅትና በትብብር ይሰራል፤
  15. የዓለም አቀፉን የፀረ-አበረታች ቅመሞች ኤጀንሲ የፀረ-አበረታች ቅመሞች ሕግ፣ ሌሎች ስምምነቶች እና የተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባህል ድርጅት የፀረ-አበረታች ቅመሞች ስምምነት ተግባራዊ እንዲሆን ያደረጋል፤ የዓለም አቀፉ የፀረ-አበረታች ቅመሞች ኤጀንሲ ዶፒንግን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ለሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎች አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል፤
  16. የዓለም አቀፉን የፀረ-አበረታች ቅመሞች ሕግ ጥሰው ከተገኙ እና የጥፋተኝነት ውሳኔ ከተላለፈባቸው ማናቸውም ግለሰቦች እና ድርጅቶች በተገኙና ለአትሌቶች፣ ለፌዴሬሽኖች እና ለስፖርት ድርጅቶች በሚሰጡ የተወሰኑ ወይም ሁሉም የገንዘብ እና ከስፖርት ጋር የሚዛመዱ ድጋፎች ላይ እገዳ ይጥላል፤
  17. በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (5) መሠረት በዓለም አቀፉ የፀረ-አበረታች ቅመሞች ሕግ መሠረት የዶፒንግ ጥሰት በመፈጸማቸው ምክንያት በአትሌቶች እና በአትሌት ደጋፊ ሠራተኞች ላይ የተጣለ የገንዘብ፣ የቁሳቁስ፣ የሰው ኃይል እና ከስፖርት ጋር የሚዛመዱ ቅጣቶች በመንግስትና በሕዝባዊ ተቋማት ተግባራዊ መደረጋቸውን ይከታተላል፤ በዓለም አቀፉ የፀረ-አበረታች ቅመሞች ሕግ አንቀጽ 10 እና 23.2.2 በግልጽ የተዘረዘሩ ውጤቶችንም ይተገብራል፤
  18. ሁሉም የመንግስት አገልግሎት ሰጭ ተቋማት እና ሌሎችም አካላት ዶፒንግን ከአገሪቱ ለማስወገድ ጠቀሜታ ያላቸውን መረጃዎች ለጽሕፈት ቤቱ እንዲሰጡ ያበረታታል፤ ይደግፋል፤
  19. በስፖርት ዶፒንግ ዙሪያ ጥናትና ምርምር ያደርጋል፣ ጥናትና ምርምር እንዲደረግም ሁኔታዎችን ያመቻቻል፤
  20. የፀረ-አበረታች ቅመሞች አስተዳደር እና ሥራ አመራር ሥርዓትን ተግባራዊ ያደርጋል፤
  21. በፀረ-አበረታች ቅመሞች ሕጉ መሠረት አድራሻ ይመዘግባል፤ የተመዘገበው የምርመራ ማህደርም በፀረ-አበረታች ቅመሞች አስተዳደርና ሥራ አመራር ሥርዓት ውስጥ እንዲያዝ ያደርጋል፤
  22. ጽሕፈት ቤቱ ባወጣው የፀረ-አበረታች ቅመሞች መመሪያ መሠረት የአትሌቶችንና የሌሎች አካላትን የግል መብት ይጠብቃል፤
  23. የተከለከሉ አበረታች ቅመሞችን ዝርዝር በተመለከተ በየጊዜው በዓለም አቀፉ የፀረ-አበረታች ቅመሞች ኤጀንሲ አማካይነት የሚደረገውን ማሻሻያ ወዲያውኑ በመቀበል ተፈፃሚ ያደርጋል፤
  24. በአገር አቀፍ ደረጃ በየእርከኑ የሚካሄደውን የፀረ-አበረታች ቅመሞች እንቅስቃሴ ገለልተኛ በሆነ መንገድ ለሚታዘቡ ታዛቢዎች ተገቢውን እውቅና ይሰጣል፤
  25. በዓለም አቀፉ የፀረ-አበረታች ቅመሞች ሕግ አንቀጽ 6.1 መሠረት የናሙና ትንተና ሲካሄድ በዓለም አቀፉ የፀረ-አበረታች ቅመሞች ኤጀንሲ እውቅና ከተሰጣቸው የምርመራ ላብራቶሪዎች መካከል ይመርጣል፤
  26. ከዶፒንግ ጋር በተያያዘ ለሚደረግ ምርመራ የሚያስፈልግ ማንኛውም ማስረጃ እንዲቀርብለት መጥሪያ መላክ፣ ምርመራ ማድረግ ወይም ማዘዝ ይችላል፤
  27. በኢትጵያ ብቸኛ የሆነ ዶፒንግን የመመርመር እና የመቆጣጠር ሥልጣኑን ተግባራዊ ያደርጋል፤
  28. ሥራዎችን በተገቢው መንገድ በማከናወን ዓላማውን ለማስፈፀም ውል ይዋዋላል፤ የንብረት ባለቤትና ባለይዞታ ይሆናል፤ በስሙ ይከሳል ይከሰሳል፤
  29. በዚህ አንቀጽ ከንዑስ አንቀጽ (1) እስከ (28) የተሰጡት ሥልጣንና ተግባራትን በዓለም አቀፉ የፀረ-አበረታች ቅመሞች ሕግ በልዩ ሁኔታ ለዓለም አቀፍ የስፖርት ፌዴሬሽኖች እና ዋና ዋና የስፖርት ኩነት የሚያዘጋጁ አካላት ከተሰጡ ሥልጣንና ተግባራት ጋር ተጣጥመው እንዲፈፀሙ ያደርጋል፡፡