ከተለያዩ ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች ለተወጣጡ የስፖርት አበረታች ቅመሞች ወይም ዶፒንግ ምርመራና ቁጥጥር ባለሞያዎች ሲሰጥ የቆየው ስልጠና ተጠናቀቀ፤ በፌዴራል ደረጃ ሲካሄድ የቆየው የስፖርተኞች ምርመራና ቁጥጥር በተቀጣይነት በተለያዩ ስፖርቶች ወደ ክልሎች እና የከተማ አስተዳደሮችም ይወርዳል፡፡

ህዳር 20/2011

የኢትዮጵያ ብሄራዊ የፀረ-አበረታች ቅመሞች ፅ/ቤት በየደረጃው የሚደካሄደው እንቅስቃሴ ቀጣይነት እንዲኖረውና ውጤታማ መሆን እንዲችል ቀደም ሲል ጀምሮ የተለያዩ ተቋማዊ የአሰራር ስርዓቶችን በመዘርጋትና ወደ ትግበራ እንዲሸጋገሩ በማድረግ ላይ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ በመስራት ላይ ይገኛል፡፡ በተለይም የስፖርተኞች ምርመራና ቁጥጥር ከፍተኛ የሆነ ፋይናንስና የሰለጠነ የሰው ኃይል የሚፈልግ ተግባር ቢሆንም ባለን ተጨባጭ አቅም ላይ ተመስርተን በየደረጃው በውድድር ጊዜም ይሁን ከውድድር ጊዜ ውጭ የስፖርተኞች ምርመራና ቁጥጥር ለማድረግ የሚያስችል ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር ሰፊ ጥረት ተደርጓል፡፡ ለዚህም ከአሁን በፊት 23 የሚሆኑ የምርመራና ቁጥጥር ባለሞያችን (DCOs, BCOs and Chaperons) በአለም አቀፍ ህጎችና ስታንዳርዶች መሰረት በማሰልጠንና Certified በማድረግ ወደ ስራ ማስገባት ተችሏል፡፡

በቀጣይም በፌዴራል ደረጃ ሲካሄድ የቆየውን የስፖርት የስፖርተኞች የአበረታች ቅመሞች ምርመራና ቁጥጥር ወደ ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች ማስፋት አስፈላጊ በመሆኑ ከተለያዩ ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች ለተወጣጡ 18 ባለሞያዎች ከህዳር 10/2011 ዓ.ም ጀምሮ በአዳማ ከተማ የንድፈ-ኃሳብ እና የተግባር ስልጠና ተሰጥቷል፡፡

ባለሞያዎቹ በስልጠናው ላይ በውድድር ጊዜና ከውድድር ጊዜ ውጭ የሚካሄደውን ምርመራና ቁጥጥር በአለም አቀፉ የፀረ-አበረታች ቅመሞች ህግ እና የምርመራና ቁጥጥር ስታንዳርድ መሰረት በአግባቡ ማከናወን የሚያስችላቸውን ግንዛቤና እውቀት ማግኘት መቻላቸው ተገልጧል፡፡

ባለሞያዎቹ ወደ ስራ ለመግባት ሞያው የሚጠይቀውን ጥብቅ ስነ-ምግባርና የስራ ቁርጠኝነት ከመላበስ ጀምሮ በተለያዩ መንገዶች ራሳቸውን ማዘጋጀት እንዳለባቸውም ተጠቁሟል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *