የስፖርት የፀረ-አበረታች ቅመሞች የህግ ጥሰት በፈፀሙ አትሌቶችና የመድኃኒት መደብር ላይ ቅጣት ተጣለ፡፡ የኢትዮጵያ ብሄራዊ የፀረ-አበረታች ቅመሞች ፅ/ቤት በጉዳዩ ላይ ከመገናኛ ብዙኃን አካላት ጋር በዛሬው ዕለት ውይይት አካሄዷል፡፡
ሰኔ 22/2010 ዓ.ም
በአገራችን ንፁህ ስፖርት ለማስፋፋትና ውጤታማነቱን ለማጎልበት በየደረጃው ዘርፈ-ብዙ እንቅስቃሴዎች በመካሄድ ላይ መሆናቸው የሚታወቅ ሲሆን በተለይም የአትሌቶች ምርመራና ቁጥጥር እንዲሁም የኢንተለጀንስና ኢንቨስቲጌሽን ተግባራት ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቷቸው እየተከናወኑ ይገኛሉ፡፡
በዚህም መሰረት ሁለት አትሌቶችና ዮሐና የተባለው የመድኃኒት መደብር የስፖርት አበረታች ቅመሞችን በመጠቀም፣ ያለ አግባብ በመሸጥና በማዘዋወር ተጠርጥረው ጉዳያቸው ሲጣራ የቆየ ሲሆን ጥፋተኛ መሆናቸው በመረጋገጡ የቅጣት ውሳኔ ተላልፏል፡፡
በመሆኑም ከአዲስ አበባ የምግብ የመድኃኒትና ጤና ክብካቤና ቁጥጥር ባለስልጣን ጋር በጋራ በመሆን በተካሄደው የኢንተለጀንስና ኢንቨስቲጌሽን ተግባር ዮሐና የመድኃኒት መደብር ቴስቴስትሮን (Testosterone) የተባለውንና በስፖርት የተከለከለውን መድኃኒት ህጋዊ ባልሆነ መንገድ ይዞ በመገኘቱ እና ያለሐኪም ትዕዛዝ ለአትሌት መሰረት ታየ አሳፍ መሸጡ በመረጋገጡ ለ2 ዓመታት ምንም አይነት መደበኛ አገልግሎት እንዳይሰጥ የታገደ ሲሆን የብቃት ማረጋገጫ ፈቃዱንም እንዲመልስ ተደርጓል፡፡
ከዚህ ባሻገር አትሌት መሰረት ታየ አሰፋ ደቡብ አፍሪካ ላይ በተካሄደው የኬፕታውን ማራቶን ላይ እ.ኤ.አ መስከረም 17/2017 በተደረገላት ምርመራ ቴስቴስትሮን (Testosterone) የተባለውን የተከለከለ አበረታች መድኃኒት መጠቀሟ በመረጋገጡ ጊዜያ እገዳ ከተጣለበት ቀን ማለትም እ.ኤ.አ ከታህሳስ 15/2017 ጀምሮ ለተከታታይ አራት ዓመታት በማንኛውም ስፖርታዊ ውድድር ላይ እንዳትሳተፍ እንዲሁም በዚህ ውድድር ያገኘቻቸው ውጤቶችና ሽልማቶች ሁሉ እንዲሰረዙ ቅጣት ተጥሎባታል፡፡
በተመሳሳይ መልኩ አትሌት መቅደስ ፈቀደ ቸገን ቻይና ላይ በተካሄደው የTai’an ማራቶን ላይ እ.ኤ.አ ሚያዝያ 23/2017 በተደረገላት ምርመራ Clenbuterol የተባለውን የተከለከለ አበረታች መድኃኒት መጠቀሟ ስለተረጋገጠ ጊዜያ እገዳ ከተጣለበት ቀን ማለትም እ.ኤ.አ ከህዳር 16/2017 ጀምሮ ለተከታታይ ሁለት ዓመታት በማንኛውም ስፖርታዊ ውድድር ላይ እንዳትሳተፍ እንዲሁም በዚህ ውድድር ያገኘቻቸው ውጤቶችና ሽልማቶች ሁሉ እንዲሰረዙ ቅጣት ተላልፎባታል፡፡
በቀጣይም በየዕርከኑ የሚካሄደው የስፖርት አበረታች ቅመሞችን የመከላከልና የመቆጣጠር ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተገልጧል፡፡