አትሌቶች ሳይዘናጉ ራሳቸውን ከኮረና ቫይረስ እና ከዶፒንግ መጠበቅ የሚገባቸው ሲሆን የኢትዮጵያ ብሄራዊ የፀረ-አበረታች ቅመሞች ፅ/ቤት አግባብ ያላቸውን የምርመራና ቁጥጥር ፕሮግራሞች ተግባራዊ ያደርጋል፡፡
በአሁኑ ወቅት አለማችንን እያስጨነቀ ያለው የኮረና ቫይረስ ወይም Covid-19 ወረርሽኝ የአገራችንም ስጋት እየሆነ መጥቷል፡፡ ከዚህም ጋር ተያይዞ ፅ/ቤታችን ለዜጎቻችን ደህንነትና ጤና ቅድሚያ በመስጠት ቀደም ሲል ጀምሮ በሰዎች መካከል ንክኪ የሚፈጥሩና ባለሞያዎችንም ሆነ አትሌቶችን ለዚህ በሽታ የሚያጋልጡ ተግባራትን ለመቀነስ ወይም ሙሉ በሙሉ ለማቋረጥ ተገድዷል፡፡
ይህን እንጅ አትሌቶች ለደቂቃም እንኳን ሳይዘናጉ ሁሌም ራሳቸውን ከስፖርት አበረታች ቅመሞች ወይም ዶፒንግ ነፃ ማድረግ የሚጠበቅባቸው ሲሆን በኢትዮጵያ ብሄራዊ የፀረ-አበረታች ቅመሞች ፅ/ቤት በኩልም የአትሌቶች ባዮሎጂካል ፓስፖርት ፕሮግራም እና የኢንተለጀንስና ኢንቨስቲጌሽን ተግባራት ትኩረት ተሰጥቷቸው ይከናወናሉ፡፡ የእያንዳንዱ አትሌት ፕሮፋይልም ቀደም ሲል ጀምሮ የተካሄዱ የምርመራ ውጤቶችንና በኋላም የሚሰበሰቡትን ናሙናዎች መሰረት በማድረግ የሚሰራ ሲሆን በመካከል የተፈፀሙ የህግ ጥሰቶችን በአግባቡ የመለየት ስራዎች በአለም አቀፉ ስታንዳርድ መሰረት ይካሄዳሉ፡፡
በዚህም መሰረት በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ለህዝባችን ደህንነትና ጤና ከመጨነቅና የበኩላችንን አስተዋፅኦ ከማድረግ ይልቅ ያልተገባ ጥቅም (Advantage) ለማግኘት በማሰብ የተከለከሉ የስፖርት አበረታች ቅመሞችን ወይም ዶፒንግ በመጠቀምም ይሁን በተለያዩ መንገዶች ምቹ ሁኔታ በመፍጠር የህግ ጥሰት የሚፈፅሙ አካላት ካሉ በአግባቡ በመለየት የእርምት እርምጃ የሚወሰድ ይሆናል፡፡
ስለሆነም እያንዳንዱ ስፖርተኛ ሳይዘናጋ ራሱን ከዚህ አስከፊ የኮረና ቫይረስ ወረርሽኝ እና ከስፖርት አበረታች ቅመሞች ወይም ዶፒንግ ሊጠብቅ ይገባል፡፡ ወረርሽኙን በመከላከልና በመቆጣጠር ረገድም የበኩሉን ገንቢ አስተዋፅኦ ማበርከት ይጠበቅበታል፡፡
አገራችንና ህዝባችንን ፈጣሪ ይጠብቅ !!!
የኢትዮጵያ ብሄራዊ የፀረ-አበረታች ቅመሞች ፅ/ቤት