የተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (UNESCO) አለም አቀፍ የፀረ-አበረታች ቅመሞች ስምምነትን (Ant-Doping convention) ለማስተግበር የተቋቋመው ኮሚቴ የጋራ ውይይት አካሄደ፡፡
ቀን ፡- 18/02/2013 ዓ.ም
አስተግባሪ ኮሚቴ የጤናውን፣ የትምህርትን፣ የፍትህን እና የስፖርቱን ሴክተር የሚመለከቱ የፌዴራል ተቋማትን ባካተተ መልኩ በአገር አቀፍ ደረጃ የተደራጀ ሲሆን በኢፌዲሪ ስፖርት ኮሚሽን ሰብሳቢነት ይመራል።
በዚህም መሠረት ኮሚቴው በዛሬው ዕለት ስብሰባውን ያካሄደ ሲሆን በስፖርት አበረታች ቅመሞች ወይም ዶፒንግ ዙሪያ የጋራ ግናዛቤ እንዲኖር እና በተቀናጀ መልኩ እንዲሰራ ለማስቻል ለኮሚቴው አባላት ገለፃ ተደርጓል። ገለፃውን ያደረጉት የኢትዮጵያ ብሔራዊ የፀረ-አበረታች ቅመሞች ጽ/ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ መኮንን ይደርሳል አገራችን ኢትዮጵያ በአለም አቀፍ ደረጃ የስፖርት አበረታች ቅመሞችን ወይም ዶፒንግን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የተባበሩት መንግስታት የትምህር፣ የሳይንስና ባህል ድርጅት የፀረ-አበረታች ቅመሞች ስምምነትን (UNESCO Ant-Doping convention) በ1999 ዓ.ም እንደተቀበለች እና በህዝብ ተወካዮች ም/ቤት አዋጅ ቁጥር 554/1999 እንደፀደቀ ተናግረዋል፡፡
ከዚህም ጋር ተያይዞ በስምምነት ሰነዱ ውስጥ በእያንዳንዱ አንቀጽ ላይ የተመላከቱ ጉዳዮችን በአግባቡ በመተግበር compliant መሆን የግድ መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል። ስለሆነም በአገራችን ያለውን አጠቃላይ እንቅስቃሴ በመገምገም አተገባበሩን የበለጠ ለማጠንከርና ክፍተቶችን ለመሙላት እንዲቻል ጉዳዩ ከሚመለከታቸው የተለያዩ ተቋማት የተወጣጡ አባላትን የያዘ ብሄራዊ ኮሚቴ (National compliance platform) በማቋቋም ወደስራ መገባቱን የጠቆሙት ዋና ዳይሬክተሩ የዚህ ኮሚቴ ሚና ክፍተኛ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
በቀጣይ ትኩረት ተሰጥቶ ሊሰራባቸው በሚገቡ የስምምነት ሰነዱ አንቀፆችና ጉዳዮች ዙሪያም በስፋት ማብራሪያ የተሠጠ ሲሆን በተለይ በአጭር ጊዜ ሊከናወኑ ከሚገባቸው ተግባራት መካከል ራሱን የቻለ የድጋፍ ስጪ ምግቦችን (Nutritional supplements ) የህግ ማዕቀፍ እንዲኖር ማስቻል፣ የሞያ ማህበራት የስነ-ምግባር መመሪያ ማውጣት፣ ጥናትና ምርምር፣ ለስራው አስፈላጊው በቂ በጀት/ፋይናስ እንዲመደብ ማድረግ የሚሉና የመሳሰሉት እንደሆነ ተጠቁሟል። ተቋማቱም በተሰጠው አቅጣጫ መሰረት የየራሳቸውን ድርሻ በመውሰድ መስራት ይጠበቅባቸዋል ተብሏል፡፡
የኢፌድሪ ስፖርት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ ዱቤ ጂሎ በበኩላቸው ዶፒንግ በአሁን ወቅት ትልቅ አለም አቀፍ ጉዳይ መሆኑን ጠቁመው በአገራችን የሚጠበቀውን ተግባር ለማከናወን ከሚቴው የማይተካ ሚና እንዳለው ገፀዋል። ስለሆነም ሁሉም ተቋማት ወሳኝ ሚና እንደሚጫወቱ ያላቸውን እምነት በመግለፅ ተቀናጅተን በጋራ በመስራት በአገራችን በዶፒንግ ዙሪያ የሚነሱ ክፍተቶችን ለማስተካከል ትልቅ አቅም ይኖረናል ብለዋል። ለዚህም በአጭር ጊዜ ወደተግባር በመግባት ስራዎችን በአግባቡ መፈፀም እንደሚገባ አሳስበዋል።