የስፖርት አበረታች ቅመም ወይም ዶፒንግ ዛሬም ትኩረት ይሻል፤ አተሌት ወንድወሰን ከተማ የተከለከለ አበረታች ንጥረ-ነገር መጠቀሙ በመረጋገጡ ቅጣት ተጥሎበታል።
   ቀን: ግንቦት 28/2012
     አትሌት ወንድሰን ከተማ ማሞ ቀደም ሲል እ.ኤ.አ ታህሳስ 01/2019 ቻይና ሻንዛቢ በተካሄደው አለም አቀፍ ግማሽ ማራቶን የግል ውድድር ላይ የተከለከለ የስፖርት አበረታች ቅመም ወይም ዶፒንግ በመጠቀም ተጠርጥሮ ላለፉት 5(አምስት) ወራት ጉዳዩ ሲጣራ ቆይቷል፡፡
ስለሆነም በተደረገው ተጨማሪ ኢንቨስቴጌሽንና የማጣራት ተግባር አትሌቱ በግሉ በተሳተፈበት ውድድር ላይ Cathinone የተባለውን በስፖርት የተከለከለ አበረታች መድኃኒት መጠቀሙ ተረጋግጧል፡፡ለዚህም አትሌቱ የፈፀመው ጥፋት የመጀመሪያ መሆኑን ግምት ውስጥ በማስገባት እ.ኤ.አ ከየካቲት 01/2020 ጀምሮ እስከ የካቲት 01/2024 ድረስ ለ4 (አራት) ዓመታት በማንኛውም አገር አቀፍም ይሁን አለም አቀፍ ውድድር ላይ እንዳይሳተፍ የእገዳ ቅጣት ተጥሎበታል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በዚህ ውድድር ላይ ብቻ ያስመዘገበው ውጤት እና ሽልማት እንዲሰረዝ ውሳኔ ተላልፏል፡፡
   በተጨማሪም ሌሎች 2 (ሁለት) አትሌቶች በተለያዩ አለም አቀፍ ውድድሮች በግላቸው በተሳተፉባቸው ስፖርታዊ ውድድሮች ላይ የተከለከሉ አበረታች ቅመሞችን መጠቀማቸው ጥርጣሬ በመኖሩ ጉዳያቸው በመጣራት ላይ ሲሆን ውሳኔው እንደተጠናቀቀ ቅጣቱንና ስም ዝርዝራቸውንም የምናሳውቅ ይሆናል፡፡
    በዚሁ አጋጣሚ ከኮረና ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ በየደረጃው የሚካሄዱት ስፖርታዊ ውድድሮች ለጊዜው የተቋረጡ ቢሆንም በአገራችን በየደረጃው የሚደረገው የስፖርት አበረታች ቅመሞች ወይም ዶፒንግ ክትትልና ቁጥጥር ግን ተጠናክሮ የሚቀጥል ሲሆን የኢትዮጵያ ብሄራዊ የፀረ-አበረታች ቅመሞች ጽ/ቤት የስፖርት አበረታች ቅመሞችን በመጠቀምም ይሁን በተለያየ መልኩ የህግ ጥሰት በሚፈፅሙ አትሌቶችና ከጀርባ ሆነው ተሳታፊ በሚሆኑ ሌሎችም ግለሰቦች ላይ የሚወስደውን የእርምት እርምጃ አጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ይገልፃል፡፡
ስለሆነም ስፖርተኞች በዚህ ክፉ ወቅት ራሳቸውን ከኮሮና ወረርሽኝ እና ከስፖርት አበረታች ቅመሞች እንዲጠብቁ ፅ/ቤቱ ጥሪውን ያስተላልፋል፡፡
                                         የኢትዮጵያ ብሄራዊ የፀረ-አበረታች ቅመሞች ፅ/ቤት