ጽ/ቤታችን /ETH-NAD0/ ከኦሮሚያ ሰፖርት ኮሚሽን ጋር እና ከአዲስ አበባ ስፖርት ኮሚሽን የጋራ /partnership/የስምምነት ውል ተፈራረመ ፡፡
ቀን ፡- 23 /11/2012 ዓ.ም
የስፖርት አበረታች ቅመሞችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በቀጣይ ያለውን ቅንጅታዊ አሰራር ተጠናክሮ መቀጠል ይገባል ተባለ፡፡
የኢትዮጲያ ብሔራዊ ፀረ-አበረታች ቅመሞች ጽ/ቤት /ETH-NAD0/ ከኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ሰፖርት ኮሚሽን እና ከአዲስ አበባ ከተማ ስፖርት ኮሚሽን በአገር አቀፍ ደረጃ ዶፒንግን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የኢንተለጀንስ እና ኢንቨስቲጌሽን ተግባር በጋራ ለመንቀሳቀስ የሚያስችለውን የፓርትነርሺፕ የውል ስምምነት ስነ-ሥርዓት የኢፌድሪ ስፖርት ኮሚሽን በተገኘበት ሐሙስ 23/2012 ዓ.ም በጽ/ቤታችን የመስብሰቢያ አዳራሽ ተፈራረሙ፡፡
ተቋማቱ የተፈራረሙት የጋራ ፓርትነርሺፕ ውል ስምምነት ዋና ዓላማ የዶፒንግ የህግ ጥሰቶችን በወንጀል ህጉን አንቀጽ 526 ላይ የተደነገገውን ተግባራዊ ለማድረግና በቀጣይ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የሚጠበቀባቸውን የክትትልና ቁጥጥር ስራው በየእርከኑ አጠናክሮ ለማስቀጠል ነው፡፡
በፓርትነርሺፑ የውል ስምምነት ሥነ-ስርዓት ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የጽ/ቤቱ ዋና ዳሬክተር አቶ መኮንን ይደርሳል እንዳሉት ጽ/ቤታችን አበረታች ቅመሞችን በመከላከልና በመቆጣጠር ንጹህ ስፖርት ለማስፋፋት እና የአገራችንንም መልካም ገፅታ ለማስቀጠል በየደረጃው ሰፊ እንቅስቃሴ በመደረግ ላይ መሆኑን ገልፀው የኢንተለጀንስ እና ኢንቨስቲጌሽን ተግባር ተዘርግቶ አበረታች ውጤት ማስመዝገብ እንደተቻለ አብራርተዋል፡፡
በፕሮግራሙ ሥነ-ስርዓት ላይ የኢፌድሪ ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ኤልያስ ሽኩር የተገኙ ሲሆን ባደርጉት ንግግር እንዲህ አይነቱ የመግባቢያ ሠነድ በስፖርቱ ላይ ጉልህ ሚና እንደሚኖረው አሰረድተው /ETH-NAD0/ በቀጣይ በሰው ሃይል ፣በቴክኖሎጂ ፣በክህሎት እንዲሁም በግብዓት መጠናከር እንዳለበት አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል ፡፡
በተጨማሪም ዶፒንግ ለመከላከልና ለመቆጣጠር የበኩሉን ድርሻ የማይወጣ የስፖርት አካል ምንም አይነት አገልግሎት እንደማያገኝ የሚመለከት አገር አቀፍ መመሪያ እየተዘጋጅ እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡
የጽ/ቤቱ ም/ዋና ዳሬክተር ወ/ሮ ፋንታዬ ገዛህኝ የኢንተለጀንስና ኢንቨስትጌሽን የስምምነት ስንድ አስመልክተው ገለፃ ያድርጉ ሲሆን የስምምነቱ ዓላማ ፣ የሚመራባቸው መርሆችና ህጎች ፣ አወቃቀሩን ከፌደራልና ከክልል ስፖርት ኮሚሽኖች በሚጠበቁ ተግባራት ዙሪያ እና የህግ ጥስት ተጠያቂነት አስመልክተው ማብራሪያ ስጥተዋል፡፡
በመግባቢያ ሰነድ ፊርማ ሥነ-ስርዓቱ ላይ የፌዴራል ስፖርት ኮሚሽን፣ የኦሮሚያ ስፖርት ኮሚሽን እና የአዲስ አበባ ስፖርት ኮሚሽን እንዲሁም የኢትዮጲያ ብሔራዊ ፀረ-አበረታች ቅመሞች ጽ/ቤት ኃላፊዎች ተሳታፊ ሆነዋል፡