ኢትዮጵያውያን አትሌቶችና የስፖርት ባለሞያዎች ከዛሬ ጀምሮ ከአሰልጣኝ አልቤርቶ ሳላዛር ጋር የሚኖራቸውን ቀጥተኛም ይሁን ቀጥተኛውን ያልሆነ ግንኙነት ማቋረጥ ይጠበቅባቸዋል። ሳላዛር በፈፀመው የፀረ-ዶፒንግ የህግ ጥሰት ለሚቀጥሉት አራት ተከታታይ አመታት በስፖርቱ ውስጥ እንዳይሳተፍ ቅጣት ተጥሎበታል።
ቀን: መስከረም 20/2012 ዓ.ም
በአለም አቀፍ ደረጃ ታዋቂ የሆነው የአትሌቲክስ ስፖርት አሠልሰጣኝ አልቤርቶ ሳላዛር የተከለከሉ አበረታች ቅመሞችን ከቦታ ቦታ ማዘዋወርን (Trafficking) ጨምሮ የፀረ-ዶፒንግ እንቅስቃሴውን በማወክ (Tampering) እና በተለያዩ የፀረ-ዶፒንግ የህግ ጥሠቶች ተጠርጥሮ ጉዳዩ በአሜሪካ የፀረ-ዶፒንግ ኤጀንሲ (USADA) ሲጣራ ቆይቷል። በዚህም መሠረት ግለሰቡ ጥፋተኛ ሆኖ በመገኘቱ ለአራት አመታት በስፖርቱ ውስጥ እንዳይሳተፍ እገዳ ተጥሎበታል።
የአለም አቀፉ የአትሌቲክስ ማህበራት ፌዴሬሽን(IAAF)ም ይህን የቅጣት ውሳኔ ለአተገባበር ያግዝ ዘንድ ለኢትዮጵያ ብሄራዊ የፀረ-አበረታች ቅመሞች ፅ/ቤት(ETH-NADO) አሳውቋል።
በመሆኑም በአለም አቀፉ የፀረ-ዶፒንግ ህግና በአገራችን የፀረ-ዶፒንግ መመሪያ አንቀፅ 2.10 መሠረት በህግ ጥሰት ቅጣት ከተላለፈባቸው ግለሰቦች ጋር ያልተገባ ግንኙት መፍጠር በጥብቅ የተከለከለ ሲሆን እስከ 2(ሁለት) ዓመት የሚደርስ ቅጣትን ያስከትላል።
ከዚህም ጋር ተያይዞ የአገራችን አትሌቶች በተለያየ መልኩ ከአሠልጣኝ አልቤርቶ ሳላዛር ጋር እንደሚሠሩ የሚታወቅ ሲሆን በግለሰቡ ላይ የተጣለው ይህ የቅጣት ውሳኔ ይፋ ከተደረገበት ጊዜ ጀምሮ ያላቸውን ቀጥተኛም ይሁን ቀጥተኛ ያልሆነ ግንኙነት እንዲያቋርጡ ፅ/ቤታችን ጥሪውን ያስተላልፋል። ከዚህ ባሻገር የስፖርት ባለሞያዎችም ይሁን ሌሎች አካላት ከዚህ ግለሠብ ጋር ያላቸውን ግንኙነት ማቋረጥ ይኖርባቸዋል።
ይህ ሳይሆን ቀርቶ ስፖርተኞችም ይሁን ሌሎች ባለሞያዎች የተቀመጠውን ህግ በመተላለፍ ቀደም ሲል የነበራቸውን ግንኙነት ለማስቀጠልና አዳዲስ ግንኙነቶችን ለመፍጠር እንቅስቃሴ የሚያደርጉ ከሆነ ፅ/ቤታችን ጉዳዩን በማጣራት አስፈላጊውን የህግ እርምጃ ለመውሰድ የሚገደድ መሆኑን ያሳውቃል።
ሁሉም አካላት የፀረ-ዶፒንግ ህጎችን በማክበርና በማስከበር ንፁህ ስፖርትን ለማስፋፋት ጥረት እናድርግ፤ የፅ/ቤታችን መልዕክት ነው።
የኢትዮጵያ ብሄራዊ የፀረ-አበረታች ቅመሞች ፅ/ቤት
(ETH-NADO)