የክብደት ማንሳት ስፖርተኞች በ12ኛው የመላ አፍሪካ ጨዋታዎች ለመሳተፍ የአበረታች ቅመሞች ወይም ዶፒንግ ምርመራ የአድራሻ (Whereabouts Information) ምዝገባ ማካሄድ ሳይችሉ ቀርተዋል።
ቀን: ነሐሴ 27/2011 ዓ.ም
በአለም አቀፉ የፀረ-አበረታች ቅመሞች ወይም ፀረ-ዶፒንግ ህግ መሠረት እያንዳንዱ ስፖርተኛ የምርመራ ቋት(Registered Testing Pool) ውስጥ መካተቱ ከተረጋገጠ ጊዜ ጀምሮ በየሶስት ወሩ የአድራሻ (Whereabouts Information) ምዝገባ ማካሄድ ይጠበቅበታል። በዚህም መሠረት በኢትዮጵያ የክብደት ማንሳት ብሄራዊ ቡድን ውስጥ የተካተቱና በመላው አፍሪካ ጨዋታ ላይ ለመሳተፍ የተመረጡ ስፖርተኞች ከግንቦት ወር 2011 ዓ.ም ጀምሮ ይህን የአድራሻ ምዝገባ ግዴታ በመወጣት ራሳቸውን ዝግጁ ማድረግ ይጠበቅባቸው ነበር።
ይሁን እንጅ የኢትዮጵያ ክብደት ማንሳት ፌዴሬሽን ቀደም ሲል የተቋቋመ ብሄራዊ ቡድን የሌለው በመሆኑና የብሄራዊ ቡድን ስፖርተኞችን የመረጠው ዘግይቶ ሐምሌ ወር 2011 ዓ.ም በተካሄደው የኢትዮጵያ ሻምፒዮና ላይ ከመሆኑ ጋር ተያይዞና በሌሎችም ምክንያቶች ስፖርተኞች ይህን የህግ ግዴታ መወጣት ሳይችሉ ቀርተዋል።
በዚህም ምክንያት የኢትዮጵያ ክብደት ማንሳት ስፖርተኞችን ጨምሮ ሌሎችም በርካታ አገሮች በ12ኛው የመላ አፍሪካ ጨዋታ ላይ እንዳይሳተፉ እገዳ ሊጣልባቸው ችሏል።
የኢትዮጵያ ብሄራዊ የፀረ-አበረታች ቅመሞች ፅ/ቤት አስፈላጊውን ምርመራና ቁጥጥር ለማካሄድ በየጊዜው ስፖርተኞችን በመምረጥ የምርመራ ቋት (Registered Testing Pool) ውስጥ የሚያስገባ መሆኑ የሚታወቅ ሲሆን ስፖርተኞችም አስፈላጊውን የአድራሻ ምዝገባ በማካሄድ በአግባቡ ግዴታቸውን መወጣት ይገባቸዋል።
በግዴለሽነትም ይሁን በተለያዩ ምክንያቶች ይህን ግዴታ በማይወጡ ስፖርተኞች ላይም እስከ ሁለት ዓመት ለሚደርስ ጊዜ ከውድድር መታገድን ጨምሮ አስፈላጊው የእርምት እርምጃ ሊወሰድ እንደሚችል መገንዘብ ያስፈልጋል።
ፅ/ቤቱም ቀጣይነት ባለው መልኩ ተገቢውን ክትትልና ቁጥጥር ከማድረግ ባለፈ ወጥ የADAMS ስርዓት በመዘርጋት አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ ላይ መሆኑን ይገልፃል።