በተለያዩ አለም አቀፍ ውድድሮች ላይ ለሚሳተፉ አትሌቶች የስፖርት አበረታች ቅመሞች ወይም የዶፒንግ ምርመራ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶት በመካሄድ ላይ ነው፡፡
የኢትዮጵያ ብሄራዊ የፀረ-አበረታች ቅመሞች ፅ/ቤት ከአለም አትሌቲክስ የኢንተግሪቲ ዩኒት(AIU) ጋር በመተባበር በአለም አቀፍ ደረጃ በተለያዩ ውድድሮች ላይ በቀጣይነት ሊሳተፉ በሚችሉ ከ150 በላይ በሚሆኑ ኤሊት ስፖርተኞች ላይ ከመስከረም 04/2013 ዓ.ም ጀምሮ የአበረታች ቅመሞች ወይም የዶፒንግ ምርመራ በማካሄድ ላይ ይገኛል፡፡
በአገራችን ንፁህ ስፖርት በማስፋፋት በየደረጃው ፍትኃዊ የውድድር ስርዓት እንዲሰፍንና በአለም አቀፍ ደረጃም ንፁህ በሆነ መልኩ ተወዳድረው የሚያሸንፉ አትሌቶችን/ስፖርተኞችን ለማፍራት ቀደም ሲል ጀምሮ ሰፊ ትኩረት ተሰጥቶት በመሰራት ላይ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ይሁን እንጅ ባለፉት ወራት በአለማችን ከተከሰተው የኮሮና (ኮቪድ-19) ወረርሽኝ ጋር ተያይዞ በየደረጃው ስፖርታዊ ውድድሮች በመቋረጣቸው የፀረ-ዶፒንግ እንቅስቃሴውም በተወሰነ መልኩ ተቀዛቅዞ ቆይቷል፡፡
ነገር ግን በአሁኑ ወቅት አለም አቀፍ ውድድሮች ቀስ በቀስ በመመለስ ላይ በመሆናቸው ይህ ጅምር እንቅስቃሴ የበለጠ መጠናከር ይጠበቅበታል፡፡ በመሆኑም የኢትዮጵያ ብሄራዊ የፀረ-አበረታች ቅመሞች ፅ/ቤት በ2013 በጀት ዓመት የምርመራና ቁጥጥር ስራውን ቀደም ሲል ከነበረው በላቀ ሁኔታ በጥራት ለማከናወን የሚያስችል እቅድ በማዘጋጀት ወደ ትግበራ ተሸጋግሯል፡፡
በዚህም መሰረት ከውድድር ጊዜ ውጭ (Out of Competition) እና በውድድር ጊዜ (In competition) የሚካሄዱ የስፖርተኞች የአበረታች ቅመሞች ወይም የዶፒንግ ምርመራ የእቅዱ ዋና ምሰሶ ሲሆን ከመስከረም 04 እስከ 05/2013 ዓ.ም ከ150 በላይ የሚሆኑ ስፖርተኞች ምርመራ ይካሄዳል፡፡ በዚህ የምርመራ ፕሮግራም ላይ በግላቸውም ይሁን አገራችንን ወክለው በተለያዩ አለም አቀፍ የውድድር መድረኮች ላይ የሚሳተፉ ኤሊት አትሌቶች/ስፖርተኞች ቅድሚያ ትኩረት ተሰጥቷቸዋል፡፡ ከ22 በላይ የኢትዮጵያ ብሄራዊ የፀረ-አበረታች ቅመሞች ፅ/ቤት (ETH-NADO) የምርመራ ባለሞያዎች(Chaperones, DCOs, BCOs) እና የምርመራ አስተባባሪዎችም ለምርመራው ስኬታማነት የበኩላቸውን ተሳትፎ በማድረግ ላይ ናቸው፡፡
ምርመራው በዋናነት የአትሌቶች ባዮሎጂካል ፓስፖርት ፕሮግራምን (ABP) በተጠናከር መንገድ ተግባራዊ በማድረግ የተከለከሉ የስፖርት አበረታች ቅመሞችን የተጠቀሙ አትሌቶችን በቀጥታ የላቦራቶሪ ትንተና ከመለየት ባሻገር የአትሌቶችን ፕሮፋይል እጅግ በጣም ሳይንሳዊ በሆነ መልኩ በተከታታይ ጥናትና ትንታኔ (Expertise Analysis) በማካሄድ በተራቀቀ መንገድ የህግ ጥሰት የሚፈፅሙትን አካላት ለመለየት የሚያስችል ስርዓት ለመዘርጋት ያስችላል፡፡
ከላይ እንደተገለፀው የአትሌቶች የምርመራና ቁጥጥር ስራ በቀጣይም ተጠናክሮ የሚቀጥል ሲሆን በ2013 በጀት ዓመት ኦሊምፒክን ጨምሮ ለተለያዩ ውድድሮች ተሳትፎ ዝግጅት የሚያደርጉ አትሌቶች በቂ የሆነ ክትትል ይደረግላቸዋል፡፡ አገራችን ኢትዮጵያም ንፁህ ስፖርተኞችን ብቻ ይዛ በአለም አቀፍ የውድድር መድረኮች የምትሳተፍበትንና ቀደም ሲል ጀምሮ የተገነባውን መልካም ገፅታ ማስቀጠል የሚቻልበትብ ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር ጥረት ይደረጋል፡፡
ለዚህም አገር አቀፍ ፌዴሬሽኖችንና የሚዲያ ተቋማትን ጨምሮ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ገንቢ ሚና እንዲጫወቱ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡