የስፖርት አበረታች ቅመሞች ወይም ዶፒንግ የህግ ጥሰት በፈፀሙ አትሌቶች ላይ የቅጣት ውሳኔ ተላለፈ፡፡
አትሌት ወንድወሰን ከተማ ማሞ እና አትሌት እዮብ ኃብተስላሴ ጎሳ የስፖርት አበረታች ቅመሞች ወይም ዶፒንግ የህግ ጥሰቶችን በመፈፀም ተጠርጥረው ላለፉት ጊዜያት ጊዜያዊ እገዳ (Provisional Suspension) ላይ ሆነው ጉዳያቸው ሲጣራ ቆይቷል፡፡
በዚህም መሰረት በተካሄደው ተጨማሪ ኢንቨስቲጌሽን አትሌት እዮብ ኃብተስላሴ ጎሳ እ.ኤ.አ የካቲት 02/2020 ዓ.ም ታይላንድ በተካሄደው ውድድር ላይ Cathinone የተባለውን የተከለከለ የስፖርት አበረታች ቅመም መጠቀሙ ተረጋግጧል፡፡ ስለሆነም አትሌቱ እ.ኤ.አ ከሚያዝያ 03/2020 ዓ.ም ጀምሮ ለተከታታይ አራት (4) አመታት በማንኛውም ውድድር ላይ እንዳይሳተፍ ቅጣት ተጥሎበታል፡፡ በውድድሩ የተገኘው ውጤትና ውጤቱን ተከትሎ የሚሰጥ የእውቅና ሽልማትም እንዲሰረዝ ተወስኗል፡፡
በተመሳሳይ መልኩ አትሌት ወንድወሰን ከተማ ማሞ ቀደም ሲል Cathinone የተባለውን የተከለከለ የስፖርት አበረታች ቅመም መጠቀሙ በመረጋገጡ እ.ኤ.አ እስከ የካቲት 01/2024 ድረስ በማንኛውም ውድድር ላይ እንዳይሳተፍ እገዳ የተጣለበት መሆኑ ይታወቃል፡፡ ይሁን እንጅ አትሌቱ የተሳሳቱ የሰነድ ማስረጃዎችን በማቅረብ የህግ ጥሰቱን የማጣራት ሂደቱን በተለያየ መልኩ በማስተጓጎልና በድጋሜ ለማጭበርበር በመሞከር ተደራራቢ የህግ ጥሰት በመፈፀም ተጠርጥሮ ጉዳዩ ሲጣራ ቆይቷል፡፡
በመሆኑም አትሌት ወንድወሰን ያቀረባቸው ሰነዶች የሐሰት መሆናቸው በመረጋገጡና በፀረ-ዶፒንግ ህጉ አንቀፅ 2.5 ላይ የተደነገገውን የፀረ-ዶፒንግ እንቅስቃሴውን የማስተጓጎልና አቅጣጫ የማሳት የህግ ጥሰት መፈፀሙ በመረጋገጡ ቀደም ሲል ከተጣለበት የአራት (4) አመት የእገዳ ቅጣት በተጨማሪ የመጀመሪያው ቅጣት ከሚያበቃበት የካቲት 01/2024 ዓ.ም ጀምሮ ለተካካታይ 8 (ስምንት) አመታት እስከ የካቲት 01/2032 ዓ.ም በማንኛውም ስፖርታዊ ውድድር ላይ እንዳይሳተፍ የእገዳ ቅጣት ተላልፎበታል፡፡
የኢትዮጵያ ብሄራዊ የፀረ-አበረታች ቅመሞች ፅ/ቤት በቀጣይም የምርመራና ቁጥጥር ስራውን አጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል፡፡