የኢትዮጵያ ብሄራዊ የፀረ-አበረታች ቅመሞች ፅ/ቤት በተለያዩ አለም አቀፍ ውድድሮች ላይ ለሚሳተፉ አትሌቶች የስፖርት አበረታች ቅመሞች ወይም የዶፒንግ ምርመራ በዛሬው እለት አካሄደ ፡፡
በተለያዩ አለም አቀፍ ውድድሮች ላይ ለሚሳተፉ ከ 30 በላይ ለሚሆኑ ኤሊት ስፖርተኞች ዛሬ ታህሳስ 06/2013 ዓ.ም የአበረታች ቅመሞች ወይም የዶፒንግ ምርመራ እየተካሄደ ነው ፡፡ ይህንን ምርመራ የኢትዮጲያ ብሔራዊ የፀረ -አበረታች ቅመሞች ጽ/ቤት ከአለም አትሌቲክስ የኢንተግሪቲ ዩኒት(AIU) ጋር በመተባበር በማካሄድ ላይ ይገኛል፡፡
በ2013 በጀት ዓመት ኦሊምፒክን ጨምሮ በተለያዩ አለም አቀፍ ውድድሮች ተሳትፎ ዝግጅት ለሚያደርጉ አትሌቶች በቂ የሆነ ክትትል እየተደረገ ነው፡፡ በዚህም መሰረት ከውድድር ጊዜ ውጭ (Out of Competition) እና በውድድር ጊዜ (In competition) የሚካሄዱ የስፖርተኞች የአበረታች ቅመሞች ወይም የዶፒንግ ምርመራ በኢትዮጵያ ብሄራዊ የፀረ-አበረታች ቅመሞች ፅ/ቤት (ETH-NADO) የምርመራ ባለሞያዎች (Chaperones, DCOs, BCOs) እና የምርመራ አስተባባሪዎች አማካኝንት ምርምራው እየተደረገ መሆኑ ተገልጻል፡፡
የኢትዮጵያ ብሄራዊ የፀረ-አበረታች ቅመሞች ፅ/ቤት በ2013 በጀት ዓመት የምርመራና ቁጥጥር ስራውን ቀደም ሲል ከነበረው በላቀ ሁኔታ በጥራት ለማከናወን የሚያስችል እቅድ በማዘጋጀት ወደ ትግበራ የገባ ሲሆን በያዝነው የበጀት ዓመት 2013 ዓ.ም መስከረም ወር ላይ ከ150 በላይ ለሚሆኑ ኤሊት ስፖርተኞች ምርመራ መደረጉ ይታወቃል ፡፡
ዶፒንግን በጋራ እንከላከል!!!!