አትሌቶች ባላቸው ወቅታዊ ብቃት፤ ጉዳት ሲያጋጥማቸው ወይም የተለየ ጥቆማ እና የኢንተለጀንስ መረጃዎችን በመሰብሰብና እነዚህን ጉዳዮች መሰረት በማድረግ በየጊዜው ከውድድር ጊዜ ውጭ (Out of Competition) የስፖርት አበረታች ቅመሞች ምርመራ ይደረግላቸዋል፡፡ ከዚህም ጋር ተያይዞ በኢትዮጵያ ብሄራዊ የፀረ-አበረታች ቅመሞች ጽ/ቤት እና አለም አቀፍ ፌዴሬሽኖች በተናጠል ወይም በጋራ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቷቸው በየሩብ አመቱ ተከታታይ የስፖርት ፀረ-አበረታች ቅመሞች ምርመራና ቁጥጥር የሚደረግላቸው ስፖርተኞችን ዝርዝር የያዘ የምርመራ ቋት (Registerd testing pool) ያቋቁማሉ፡፡

እያንዳንዱ አትሌት በአገር አቀፍም ይሁን በአለም አቀፍ ደረጃ በተለያዩ የስፖርት ማህበራት የምርመራ ቋት(Registerd testing pool) ውሰጥ ከተካተተ የማሳወቂያ ደብዳቤ (notification letter) በፌዴሬሽኑ በኩል ወይም በራሱ ኢ-ሜይል እንዲደርሰው የሚደረግ ሲሆን አትሌቱ አስፈላጊውን ሂደት በማጠናቀቅ የአድራሻ ምዝገባ (Whereabouts information) ያካሂዳል፡፡

እያንዳንዱ አትሌት በሚሞላው አድራሻ መሰረት በየጊዜው የስፖርት አበረታች ቅመሞች ምርመራ የሚደረግለት ሲሆን በምርመራ ቋት ውስጥ ከተካተተ ከሶስት ወር በኋላ በድጋሚ በምርመራ ቋቱ ውስጥ ሊቀጥል ወይም ሊወጣ ይችላል፡፡

ማንኛውም አትሌት በተለያዩ ምክንያቶች ውድድር በሚያቆምበት ወቅት የምርመራ ቋት ውስጥ የማይካተት በመሆኑ ውድድር ማቆሙን ለሚመለከተው አካል ማሳወቅ የሚኖርበት ሲሆን ወደ ውድድር ሲመለስም በድጋሜ መመለሱን ለሚመለከተው አካል ማሳወቅ ወይም ሪፖርት ማድረግ ይኖርበታል፡፡